Search

ኢትዮጵያ በ17ኛው የተባበሩት መንግሥታት የብዝሃ ህይወት ጉባኤ አረንጓዴ ተሞክሮዋን እያስተዋወቀች ነው

ቅዳሜ ጥቅምት 14, 2019 54

 ኢትዮጵያ በአርሜንያ አዘጋጅነት በሬቫን ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው 17ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የብዝሃ ህይወት ጉባኤ (COP17) ላይ በብዝሃ ህይወት ጥበቃ ዘርፍ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶችና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተሞክሮዎች በማስተዋወቅ ላይ ትገኛለች።

ጉባኤው በአውሮፓውያኑ 2022 የፀደቀውን የኩንሚንግ ሞንትሪያል ዓለም አቀፍ የብዝሃ ህይወት ማዕቀፍ አፈፃፀም (ከ2020 እስከ 2030) የብዝሃ ህይወት መመናመንን ለማስቆም እና ወደነበረበት ለመመለስ ባስቀመጣቸው ግቦች ላይ ያተኮረ ነው።

የኢትዮጵያን ልዑክ በመመራት በጉባኤው ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት የስራ ሃላፊ አቶ ተስፉ ፈቀንሳ እንደገለፁት፣ ሀገራችን ባለፉት ሰባት አመታት ገደማ ወደ 56 ቢሊዮን የሚጠጉ ችግኞችን በመትከል ያከናወነችውን ታላቁን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተሞክሮ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በማካፈል ላይ ትገኛለች።

ህብረተሰቡን ማዕከል ያደረገው ይህ የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ የተጎዱ ስነ ምህዳሮችን በመመለስ፣ የብዝሃ ህይወትን በማጠናከር እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ድርድሮችና መድረኮች ላይ ያላትን መሪነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት የበለጠ ለማሳደግ 19ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የብዝሃ ህይወት ጉባኤ በአዲስ አበባ ለማስተናገድ ጥያቄ አቅርባለች።

የኢትዮጵያ የብዝሃ ህይወት ስትራቴጂ ጥበቃ የሚደረግላቸውን ቦታዎች ማስፋፋት፣ የተጎዱ ስነ ምህዳሮችን ማጠናከር እና ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የሚሆኑ ሀብቶችን ማሰባሰብን ጨምሮ ከአለም አቀፉ ማእቀፍ ግቦች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣጣም ነው።

ይህ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የአካባቢ ጥበቃ መሪነት፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ዓለምን የምታስደምም #ትልቅሀገር፣ የተፈጥሮ ሀብቱን በፍቅርና በትጋት የሚንከባከብ #ትልቅሕዝብ እንዲሁም ለዘላቂ ሥነ-ምህዳርና የአየር ንብረት ፍትህ የሚታገል #ታላቅርዕይ ያላት ሀገር መሆኗን ማረጋገጫ ነው።

በብሌን ደምበሎ

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: