Search

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ፡- ከዲፕሎማሲያዊ ጥረት እስከ ባሕር ኃይል ግንባታ

ማክሰኞ ጥቅምት 17, 2019 202

ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋን እውን ለማድረግ የዲፕሎማሲ ጥረቷን እያጠናከረች የባሕር ኃይሏን መልሳ በማቋቋም የቀጣናውን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ አቅሟን ለማሳደግ እየሠራች ትገኛለች።

የባሕር በር ጉዳይ ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር ከብሔራዊ ጥቅም እና ከሀገራዊ ሕልውና ጋር የተያያዘ ጉዳይ መሆኑን የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አመራሮች ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ካፒቴን ዝናቡ ዘንጌ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ባሕር በርን ማንሳትና የባሕር ኃይልን ማቋቋም ቀደም ሲል ወደ ግጭት እንደሚያመራ ይታሰብ እንደነበረ አስታውሰው፣ አሁን ላይ ይህ አመለካከት መቀየሩን ገልጸዋል።

የባሕር በር ጥያቄ ብሔራዊ ጥቅምና የሕልውና ጉዳይ መሆኑ በይፋ መነሳቱን ጠቅሰው፣ የዲፕሎማሲ ሥራውም ተጠናክሮ እየቀጠለ መሆኑን አስረድተዋል።

በቅርቡ የባሕር በር ለማግኘት የሚደረገው ጥረት እውን እንደሚሆን የሚያመለክቱ ሁኔታዎች እንዳሉም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ዋና አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በፖለቲካዊ ሂደቶች ምክንያት ያጣችውን ወደብ መልሳ የማግኘት ጥያቄ እያቀረበች መሆኗን ዓለም እየተረዳ መምጣቱን ገልጸዋል።

የባሕር በር ጥያቄውን እውን ማድረግ የትውልድ ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም የባሕር ኃይሉ የሰው ኃይልና የሙያ አቅም በማጠናከር ላይ መሆኑን አመልክተዋል።

ዋና አዛዡ እንደገለጹት፣ የሀገራችን ጥቅም በአሰብ ወደብ ብቻ የተገደበ አይደለም፤ በቀይ ባሕር፣ በሕንድ ውቅያኖስ እና ከዚያም ባሻገር ባሉ ዓለም አቀፍ የውሃ አካላት ላይ ሀገራችን የንግድና የደኅንነት ጥቅሞች አሏት፤ እነዚህን ጥቅሞች በሰላማዊ መንገድ ለማስከበር የሚደረገው ዝግጅት እየተጠናከረ ነው።

ኢትዮጵያ አውሮፓ ሕብረትን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት ጋር በምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ የባሕር በር ጥያቄዋንና ታሪካዊ ዳራውን የማስረዳት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

የባሕር በር ማግኘት ጥያቄ ከባሕር ኃይል ግንባታ ጋር ተያይዞ የንግድ መርከቦችን እና የባሕር ላይ የኢኮኖሚ ጥቅሞችን የመጠበቅ ጉዳይንም ያካትታል ያሉት ዋና አዛዡ፣ ኢትዮጵያ በንግድ መርከቦች ላይ ያላት ተሳትፎ የባሕር ኃይል አቅሟን ማሳደግና በውሃ አካላት ላይ ያላትን ጥቅም ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የባሕር ኃይሉ ዕድገት ከሀገራችን አጠቃላይ የመከላከያ አቅም አንዱ አካል መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላት አቅም የባሕር ኃይልን ብቻ ሳይሆን የሌሎች የደኅንነት ዘርፎችንም እንደሚያካትት አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና በምስራቅ አፍሪካ የሰላም ማስከበር ሥራዎች የረጅም ጊዜ ልምድ ያላት ሀገር ናት። በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ያላት ተሳትፎ፣ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ የሚኖራትን አስተዋጽኦ ያሳያል። የባሕር ኃይሉ መጠናከርም ከዚህ አጠቃላይ የደኅንነት አቅም ግንባታ ጋር የተያያዘ ነው።

የባሕር በር ጥያቄ፣ የባሕር ኃይል ግንባታ እና ቀጣናዊ የሰላም ማስከበር አቅም የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ፣ የደኅንነትና የዲፕሎማሲ ጥቅሞች ከማስጠበቅ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው።

የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማስከበር የሚደረገው ጥረት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚቀጥል ኃላፊነት መሆኑንም አመራሮቹ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በኢንቲሃድ አብራር

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: