Search

የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ፡- ከሶቺው እስከ ሞስኮው የ2029 ስትራቴጂካዊ ፍኖተ ካርታ

ረቡዕ ጥቅምት 18, 2019 205

የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ፣ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የሶቪየት ኅብረት ለአፍሪካ የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግልና አዲስ ነፃ ለወጡ መንግሥታት የኢንዱስትሪና የማኅበራዊ ተቋማት ግንባታ ካደረገችው ታሪካዊ ድጋፍ የሚመዘዝ ጥልቅ ዳራ አለው።

የመጀመሪያው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ከጥቅምት 23 እስከ 24 ቀን 2019 (እ.ኤ.አ.) በሶቺ ከተማ "ለሰላም፣ ለደህንነት እና ለልማት" በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል።

ይህም በዘመናዊቷ ሩሲያ ታሪክ እንዲህ ዓይነት ሰፊ ሁነት ሲዘጋጅ የመጀመሪያው የነበረ ሲሆን፣ በሩሲያና አፍሪካ ግንኙነት ውስጥም ታይቶ የማይታወቅ ነበር። ተሳታፊዎቹ በሚቀጥሉት ዓመታት ተጨባጭ ውጤቶች ሊመዘገቡባቸው የሚችሉ ቀዳሚ የኢኮኖሚ ትብብር መስኮችን ለይተዋል።

የ54ቱንም የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮችና ከ40 በላይ መሪዎችን ያሰባሰበው ይህ መድረክ፣ የሩሲያን የውጭ ፖሊሲ ወደ ፓን-አፍሪካዊ ማዕቀፍ በማሳደግና የሩሲያ-አፍሪካ አጋርነት ፎረምን በመመሥረት፤ ከርዕዮተ ዓለም ጫና እና ከአዲስ ቅኝ አገዛዝ (ኒዮ-ኮሎኒያሊዝም) ነፃ የሆነ፣ በእኩልነትና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ባለብዙወገን ዋልታ የዓለም ሥርዓትን ከ"ዓለም አቀፉ ብዙኃን" ጋር የመገንባት ዓላማ ሰንቆ የተነሳ ነበር።

ከሶቺው መሠረት በመነሳት በሐምሌ 2023 በሴንት ፒተርስበርግ የተካሄደው ሁለተኛው ጉባኤ፣ ግንኙነቱን ከዲፕሎማሲያዊ ንግግር ወደ ተቋማዊና ተግባራዊ ስትራቴጂ የቀየረ ነበር። በጉባኤው የጸደቀው ባለ 74 ነጥብ የጋራ መግለጫ እና 181 ነጥቦችን የያዘው ከ2023–2026 የድርጊት መርሐ ግብር፤ ሕገ-ወጥ የአንድ ወገን ማዕቀቦችን መቃወምን፣ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት የአፍሪካን ውክልና ማረጋገጥን፣ የዓለም አቀፉን የፋይናንስ መዋቅር ማሻሻልን እንዲሁም ከምዕራባውያን ተጽዕኖ ነፃ የሆኑ የባንክ ክፍያ፣ የኢንሹራንስና የሎጂስቲክስ ሥርዓቶችን መዘርጋት ላይ አተኩሯል።

በእነዚህ ውሳኔዎች በ2024 በሶቺና በ2025 በካይሮ በተካሄዱት የሚኒስትሮች ኮንፈረንሶች እንዲሁም በሐምሌ 2026 በአዲስ አበባ በሰርጌይ ላቭሮቭ እና በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ መካከል በተደረገው ምክክር ታግዞ፣ የሁለቱ ወገኖች የንግድ ልውውጥ በ2019 ከነበረበት 16.8 ቢሊዮን ዶላር በ2025 ወደ 27.1 ቢሊዮን ዶላር አድጓል።

ይሁንና የሩሲያ የወጪ ንግድ 22.7 ቢሊዮን ዶላር ሆኖ የአፍሪካ ድርሻ 4.4 ቢሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑ የሚፈጥረውን የንግድ ሚዛን መዛባት ለማረም፣ ትብብሩ በአፍሪካ ውስጥ የማምረትና እሴት የመጨመር አቅምን ወደ መገንባት እንዲሸጋገር ግድ ብሏል።

ዛሬ ጥቅምት 28 ቀን 2026 በሞስኮ የተጀመረውና የ48 የአፍሪካ ሀገራት ልዑካንና 22 የሀገር መሪዎች የሚሳተፉበት ሦስተኛው ጉባኤ ያለፉትን ሰባት ዓመታት የፖሊሲ አፈጻጸም በመገምገም የ2027–2029 አዲስ የድርጊት መርሐ ግብር የሚያጸድቅበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው።

በፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን እና በአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ በጋራ የሚመራው ይህ ጉባኤ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ሰላማዊ አጠቃቀም ላይ ልዩ መግለጫ የሚያወጣ ሲሆን "የሉዓላዊነት ማስጠበቂያ መሣሪያዎች" ተብለው በሚጠሩት የዲጂታል መረጃን በሀገር ውስጥ ማከማቸት፣ የኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት አገልግሎት፣ የሳተላይትና የፋይበር ኦፕቲክ መሠረተ ልማት፣ የጂኦሎጂካል ጥናት፣ የኒውክሌር እና የታዳሽ ኢነርጂ እንዲሁም የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ዘርፎች ላይ ልዩ ትኩረት አድርጓል።

በዚህ ስትራቴጂካዊ ምኅዳር ውስጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በእጅጉ የሚጎላበት ሰፊ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድል ተፈጥሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሞስኮው ጉባኤ ጎን ለጎን ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር የሚያደርጉት የሁለትዮሽ ውይይት፣ ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ ኅብረት መቀመጫነቷና እንደ ቀጣናዊ መልህቅ  ሀገር በሩሲያ የውጭ ፖሊሲ ውስጥ ያላትን ክብደት ያሳያል።

ኢትዮጵያ ከግብፅና ከደቡብ አፍሪካ ጋር የብሪክስ (BRICS) ሙሉ አባል መሆኗ፣ የውጭ ግንኙነት አማራጮቿን በማስፋት፣ በሰብዓዊ መብትና በአካባቢ ጥበቃ ስም የሚጣሉ ፖለቲካዊ ቅድመ ሁኔታዎችንና የአንድ ወገን ጫናዎችን በመመከት እንዲሁም የዕዳ ጫናን የሚያቃልል ፍትሐዊ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ መዋቅር እንዲፈጠር በሚደረገው ትግል ውስጥ ወሳኝ ድምፅ እንዲኖራት ያስችላታል።

ከኢኮኖሚያዊና ቴክኖሎጂያዊ ጥቅም አንጻርም፣ ሩሲያ ከቀጥተኛ የእህል አቅርቦት ባለፈ በአፍሪካ ውስጥ የማዳበሪያ ምርትን፣ የግብርና ሜካናይዜሽንን፣ የምርጥ ዘር ብዜትንና የአየር ንብረት አደጋዎች ትንበያ ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት የያዘችው አቅጣጫ፣ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥና ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ከምታደርገው ጥረት ጋር በቀጥታ ይጣጣማል።

በተጨማሪም በኒውክሌርና በንጹሕ ኢነርጂ ልማት፣ በዲጂታል ኢኮኖሚና በሳይበር ደህንነት የሚደረገው የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በሩሲያ ዩኒቨርሲቲዎች በሕክምና፣ በኢነርጂና በምሕንድስና መስኮች የሚሰጠው የባለሙያዎች ሥልጠና ከኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶች ጋር ሲተሳሰር ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል።

ከሁሉም በላይ ሩሲያን በኢራን እና በሕንድ በኩል ከምሥራቅ አፍሪካ ጋር የሚያገናኘው የሰሜን-ደቡብ የትራንስፖርት ኮሪደር እውን መሆን፣ ከአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) እና ከአጀንዳ 2063 ጋር ተዳምሮ ለኢትዮጵያ አማራጭ የንግድ፣ የኢንዱስትሪና የሎጂስቲክስ በር በመክፈት ብሔራዊ ጥቅሟን በዘላቂነት የሚያስጠብቅ ስትራቴጂካዊ አቅም ይፈጥራል።

 

በበረከት ሽመልስ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: