የቻይና ሁቤይ ግዛት የዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና የጥንታዊ ቅርስ አዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራን ለዓለም አብስራለች። ይህች የቻይና ግዛት በታሪካዊ ስፍራነቷ በብሔራዊ ደረጃ የ4A ደረጃ የተሰጣት ዝነኛዋ የጂንግዙ ጥንታዊ ከተማ በመባል ትታወቃለች።
በከተማዋ በብዛት ሰዎች በሚበዙበትና የትራፊክ ፍሰት በሚበዛበት የምስራቅ በር መግቢያ መስቀለኛ መንገድ ላይ "ሺያኦአን" የተሰኘ ይህ የትራፊክ ፖሊስ ሮቦት ከሰው ትራፊክ ፖሊሶች ጎን በመሰለፍ ተሽከርካሪዎችን እና እግረኞችን በብቃት ማስተናገዱ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል።
ቁመቱ 1.73 ሜትር የሚሆነው ይህ ዘመናዊ ሮቦት ከትራፊክ መብራቶች ጋር በመናበብ እና በተለመዱ የእጅ ምልክቶች ተሽከርካሪዎችን በትክክለኛው አቅጣጫ ይመራል።
በዚህም በበዓላትና በእረፍት ቀናት ላይ ከፍተኛ የጎብኚዎች ቁጥር ወደ ከተማዋ ሲጎርፍ የሚፈጠረውን የትራፊክ ጫና ማቃለል ችሏል። ከዚህም አልፎ ሳይደክም ረጅም ሰዓታትን በሥራ ላይ በመቆየት የሰው ኃይል ክፍተቶችን የሚሸፍን ሲሆን፣ በተጨማሪም በድምፅ ማሳሰቢያ መልእክት አሽከርካሪዎችና እግረኞች የትራፊክ ሕጎችን እንዲያከብሩ ያስታውሳል።
የጂንግዙ ከተማ የትራፊክ አስተዳደር እንደሚያስረዱት፣ አካባቢው የተሽከርካሪና የእግረኛ መጋፋት ስለሚበዛበት ሮቦቱ ያለመታከት ለረጅም ሰዓታት በመቆም የትራፊክ ፖሊሶችን የሥራ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ ቀንስቷል።
"ሺያኦአን" የትራፊክ ፍሰቱን ከመምራት ባለፈ ሕግ ተላላፊዎችን ወዲያውኑ የመለየት ድንቅ ብቃት እንዳለው አስተዳዳሪው አክለው ገልጸዋል። ለምሳሌ ያህል የትራፊክ ፍሰቱ በተጣበበበት ሰዓት የደህንነት መጠበቂያ ሄልሜት ሳያደርግ በኤሌክትሪክ ብስክሌት የተጓዘውን አንድ አሽከርካሪ በድምፅ በማስጠንቀቅ ሕጉን እንዲያከብር ያደረገበት አግባብ ቴክኖሎጂው ለደህንነት ያለውን ፋይዳ በግልጽ አሳይቷል።
በተጨማሪም ሮቦቱ የብስክሌትና የኤሌክትሪክ ብስክሌት አሽከርካሪዎች የቆመ መስመር ሲያልፉ ወይም እግረኞች የቀይ መብራት እያለ ሲሻገሩ የመቆጣጠር አቅም አለው።
ይህ ሮቦት የበርካታ የአካባቢው አላፊ አግዳሚዎችን፣ የሕፃናትን እና የቱሪስቶችን ትኩረት በመሳብ በርካቶች አብረውት ፎቶ ሲነሱና ሲጫወቱ ታይተዋል። ይህ የግዛቲቱ ድንቅ ስሪት የሰውን ልጅ የፈጠራ አቅም ከቴክኖሎጂ ቅልጥፍና ጋር በማቀናጀት በመሰራቱ ለትራፊክ ፖሊሶች እና ለአሽከርካሪዎች ትልቅ እፎይታ መሆኑ ተመላክቷል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: