በትግራይ ክልል ከጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ከመደበኛው ሥርዓት የወጣውን የትራንስፖርት ፍሰት ወደ ሕጋዊ አሠራር ለመመለስ የትራፊክ ፖሊሶች ወደ ሥራ ተመልሰዋል።
ይህም በተለይ በዋና ከተማዋ መቐለ የትራፊክ ፍሰቱን እና የንግድ እንቅስቃሴውን እያሳለጠው መሆኑ ተገልጿል።
በክልሉ በነበሩ የጸጥታ ችግሮች በመቐለ ከተማ የትራንስፖርት ሥርዓቱ መዳከሙንና ያለ ሕጋዊ ሰነድ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች መበራከታቸውን ትራፊክ ፖሊሶች ገልጸዋል።
ይህም ለትራፊክ አደጋዎችና ለተለያዩ ወንጀሎች መከሰት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
ምክትል ኮማንደር ጣዕመ በርኸ እንደገለጹት፣ በተለይ ያለ ታርጋ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችና ያለ መንጃ ፈቃድ የሚነዱ አሽከርካሪዎች በርክተው ነበር።
ሳጅን አብርሃም ካሱ በበኩላቸው፣ የትራፊክ አደጋዎችን ጨምሮ የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች መበራከታቸው ማኅበረሰቡን ለተለያዩ ችግሮች ዳርጎ እንደነበር አስረድተዋል።
አሁን ትራፊክ ፖሊሶች ወደ ሥራ በመመለሳቸው፣ አሽከርካሪዎች የትራፊክ ሕግና ሥርዓትን እንዲያከብሩ የማስተማርና የማስገንዘብ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አክለዋል።
ትራፊክ ፖሊሶቹ በጎዳናዎች በመሰማራት የትራንስፖርት ፍሰቱን ከማሳለጥ ባለፈ፣ ከአደጋ ነፃ የሆነ የመንገድ አጠቃቀምን ለማስፈን እየሠሩ መሆኑን ሳጅን ማዕረግ አሰፋ ገልጸዋል።
የትራፊክ ፖሊስ አባላቱ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደተመለሱ የገለጹት ሳጅን ማዕረግ፣ አሽከርካሪዎችን በማስተማርና ሕጋዊ ሥርዓትን በማስከበር ሥራቸውን መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም ማኅበረሰቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲመለስ፣ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
የትራፊክ ፖሊሶች ወደ ሥራ መመለስ በመቐለ የንግድ እንቅስቃሴ ላይም አዎንታዊ ለውጥ እያስገኘ መሆኑን የከተማዋ ነጋዴዎች ገልጸዋል።
በጸጥታ ስጋት ምክንያት ተዘግተው የቆዩ የንግድ ቦታዎች እንደገና መከፈታቸውንና የገበያ እንቅስቃሴው እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመዋል።
የፖሊስ አባላት ወደ ሥራ መግባታቸው ከጸጥታና ደህንነት አንጻር በነዋሪዎች ዘንድ መተማመን በመፍጠሩ፣ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ነጋዴዎች ድርጅቶቻቸውን መልሰው እየከፈቱ መሆናቸው ተገልጿል።
በክልሉ የሕግ የበላይነትን በማስከበርና የተገኘውን ሰላም በማጽናት የሕዝብን እንቅስቃሴ ማሳለጥ ለዘላቂ ደህንነትና ልማት ወሳኝ መሆኑ ታምኖበት በዚሁ አግባብ እየተሠራ መሆኑ ተመላክቷል።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: