የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "የመደመር" መጽሐፍ ወደ ሩሲያኛ ቋንቋ ተተርጉሞ በሞስኮ ለንባብ የበቃ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተዘጋጀው የመጽሐፉ የምረቃ መርሃ ግብር ላይ በአካል ተገኝተው በመካፈላቸው ታላቅ ደስታና ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
ይህ ታሪካዊ ስኬት የመደመር ፍልስፍና ከኢትዮጵያ አገር በቀል እውቀት ተነስቶ ዛሬ ላይ ድንበር በመሻገር ወደ መላው ዓለም እየሰፋ መሄዱን የሚያሳይ ህያው ማረጋገጫ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አብራርተዋል።
ከዚህ በፊት መጽሐፉ ከአገር ውስጥ ቋንቋዎች በተጨማሪ በእንግሊዝኛ፣ በቻይንኛ እና በአረብኛ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለብዙኃን አንባቢያን መድረሱ ይታወሳል።
አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ሀሳብ ድንበር ተሻግሮ በሰፊው የሩሲያኛ ተናጋሪ ደጃፍ መድረሱ የፍልስፍናውን ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነትና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ ይበልጥ እንደሚያጎለብተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ይህ እርምጃ የመደመርን ፍልስፍና፣ እሴቶችና ሀሳቦች ከኢትዮጵያ አልፈው ለሌሎች ሕዝቦች የሚደርሱበትን አዲስ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ፣ ኢትዮጵያ ለዓለም የምታበረክተው የራሷ የበሰለ ሀሳብ እንዳላት በተግባር የሚያሳይ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ሩሲያ ለብዙ ኢትዮጵያውያን የሥነ ጽሑፍና የዕውቀት መማሪያ ምድር ሆና እንዳገለገለች ሁሉ፣ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ሀሳብ በሩሲያኛ ቋንቋ ለሩሲያ አንባቢያን መድረሱ የዕውቀት ልውውጡን ሙሉ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
ለዚህ ስኬት መሳካትና ለመጽሐፉ ዝግጅት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱትን የሩሲያ ቱዴይ (RT) የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና አመራሮች ያደረጉትን ጥረትና ትጋት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አድንቀዋል።
ይህ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ የኢትዮጵያን የበለጸጉ አገር በቀል እውቀቶች፣ ባህሎችና ፍልስፍናዎች በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ይበልጥ ለማስተዋወቅና በሕዝቦች መካከል ጠንካራ የባህልና የሃሳብ ድልድይ ለመገንባት የሚኖረው ሚና እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ታምኖበታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: