Search

በድሮን ብቻ ሳይሆን በSu-30 እና በSu-35 አቅም መገንባት ያስፈልገናል፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ረቡዕ ጥቅምት 18, 2019 99
ኢትዮጵያ የአየር ክልሏን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ እና በቀጣናው የአየር የበላይነትን ለመጎናጸፍ የሚያስችሏትን የ4++ ትውልድ የሆኑ የSu-35 ተዋጊ አውሮፕላኖችን የመጀመሪያ ዙር መረከቧን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
በዚህም ኢትዮጵያ ይህንን ዘመናዊ የውጊያ ቴክኖሎጂ በመታጠቅ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የመጀመሪያዋ ሀገር መሆን ችላለች።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአየር ኃይሉን አዲስ ትጥቅ አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ያለውን የአየር ኃይል የቴክኖሎጂ ሩጫ እና በሀገራችን ላይ የተጋረጡ ስጋቶችን በመገንዘብ ከሩሲያ መንግሥት ጋር የSu-35 ተዋጊ ጄቶችን እና የS-400 የአየር መከላከያ ሲስተም ግዥ ስምምነት ከጥቂት ዓመታት በፊት መፈራረሟን አስታውሰዋል።
በስምምነቱ መሠረት በመጀመሪያው ዙር 12 የSu-35 ተዋጊ አውሮፕላኖች እና አራት ባትሪ የS-400 የአየር መከላከያ ሲስተም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ዙር ርክክብም በስኬት ተከናውኗል።
በዓለም ላይ ምርጥ የሚባለውን የዘመኑን ቴክኖሎጂ የታጠቀውና በተግባር የተፈተነው የSu-35 ተዋጊ አውሮፕላን፣ ከአየር-ወደ-አየር እና ከአየር-ወደ-ምድር የመዋጋት ከፍተኛ ብቃት አለው። በተለይም ከየትኛውም አቅጣጫ የሚላኩ የክሩዝ ሚሳይሎችን እስከ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ አስቀድሞ የመለየት እና አየር ላይ የማምከን አቅሙ የተረጋገጠ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
"በድሮን ብቻ ሳይሆን በSu-30 እና በSu-35 የ4ኛ እና የ4++ ትውልድ አቅም መገንባት ያስፈልገናል፤ ምክንያቱም ራቅ ካለ አካባቢ የሚቃጡ ሙከራዎች ካሉ ለመግታት ስለሚያግዝ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ይህ አዲሱ ትጥቅ ቀደም ሲል ከነበሩት የSu-30 አውሮፕላኖች ጋር ተደምሮ የኢትዮጵያን የአየር ክልል በበቂ ሁኔታ ለመከላከል እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ከተዋጊ ጄቶቹ በተጨማሪ የS-400 የአየር መከላከያ ሲስተም ሙሉ በሙሉ ወደ ስምሪት ሲገባ፣ ሀገራችን ክሩዝ ሚሳይሎችን ብቻ ሳይሆን የባሊስቲክ ሚሳይሎችንም አየር ላይ የማምከን አቅሟ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያድግ ተመላክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አክለውም ባለፉት ጊዜያት ይህንኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚያንቀሳቅሱ ባለሙያዎችን የማሰልጠን ሥራ ሲከናወን መቆየቱን ጠቅሰው ኢትዮጵያ የማጥቃት ብቻ ሳይሆን የአየር መከላከያ ሲስተሟን የማሳደግ ሥራዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
በበረከት ሽመልስ
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: