በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአንድ ሀገር ብሔራዊ ደኅንነትና ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው በጦር ሜዳ ላይ በሚደረግ የኃይል ግብግብ ብቻ አይደለም። ይልቁንም ሀገራት ስጋቶችን ቀድመው የመለየት፣ የመተንተን፣ ጠላት ጥቃት የማድረስ ፍላጎት እንኳ እንዳይኖረው የሚያደርግ አስተማማኝ የቅድመ-መከላከል (Deterrence) አቅም የመገንባት ጥበባቸው ዋናው የሕልውናቸው መለኪያ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያካሄደው አጠቃላይ ተቋማዊ ሪፎርም፣ የሰው ኃይል ማዘመን፣ የቴክኖሎጂ ባለቤትነት እና የትጥቅ ዝግጁነት ሀገራችንን ወደ አዲስ የመከላከል እና የብቃት ምዕራፍ አሸጋግሯታል።
በዘመናዊ የፖለቲካና የመከላከያ ሳይንስ፣ ጠንካራ የመከላከል አቅም መገንባት ለጦርነት መዘጋጀት ሳይሆን አስተማማኝ ሰላምን የመግዛት ጥበብ ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የዝግጁነት ግንባታ መሠረታዊ ፍልስፍና ሀገራችንን ወደ ውጊያ ማስገባት ሳይሆን ጥቃት አድራሾች ወደ ጥቃት እንዳይገቡ ቀድሞ የኃይል ሚዛንን ማስጠበቅ ነው።
ይህ የቅድመ-መከላከል አቅም ጠላት ጥቃት ለመፈጸም የሚያደርገውን ዝግጅት ወይም ፍላጎት ከመነሻው የሚያስቀር ሲሆን የጥቃቱ ዋጋ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች በላይ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን እንዲገነዘብ ያደርጋል።
ጠንካራና ጀግና መከላከያ ሀገራዊ ልማትና የኢኮኖሚ እድገት ያለ ስጋት እንዲከናወኑ የሚያስችል አስተማማኝ ከለላ ይሰጣል።
ዘመናዊ ውጊያዎች እና ጥቃቶች ባህርያቸውን በመቀየራቸው የመከላከያ አቅም የሚለካው በተዋጊዎች ብዛት ብቻ አይደለም።
የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ትኩረት ያደረገው በተቀናጀና የላቀ የቴክኖሎጂ ሥርዓት በተደገፈ የውጊያ ዝግጁነት ላይ ነው።
የመከላከያ ሠራዊት ጥንካሬ የሚለካውም በሠራዊቱ ሥነ-ምግባር፣ የትምህርት ዝግጅት፣ ተቋማዊ ገለልተኝነት እና በማይናወጥ ጀግንነት ነው።
ሠራዊቱን በሥነ-ልቦና፣ በታክቲክ፣ በስትራቴጂያዊ አስተሳሰብ እና በህግ ማዕቀፎች የማሠልጠን ሥራዎች በከፍተኛ ትኩረት ተከናውነዋል።
መከላከያ ሠራዊቱ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መገለጫና ለህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱና ለሀገር ሉዓላዊነት ብቻ የታመነ ወታደራዊ ተቋም ሆኖ እንዲደራጅ ተደርጓል።
እንዲሁም የራስን የቴክኖሎጂና የሎጂስቲክስ አቅም በሀገር ውስጥ ደረጃ የማደራጀትና የማበልጸግ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ይህ የመከላከያ አቅም ግንባታ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም፣ ከምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ መረጋጋት እና ከመደመር ፍልስፍና የተቋማት ግንባታ ራዕይ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያለው ነው።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት እያከናወነ ያለው የዝግጁነት ግንባታ ሀገራችንን ከቀጣናው አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭነት ያለውን ስትራቴጂካዊ አቅም አላብሷታል።
የሠራዊቱ ጥንካሬ በሚያሳየው የሰላም ዋስትና፣ ስጋቶችን ቀድሞ በማክሸፍ፣ ሉዓላዊነትን በማስከበር እና ለቀጣናዊ መረጋጋት በሚያበረክተው የማይናወጥ ሚና የሚለካ ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: