Search

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከታሪካዊ ጀግንነት እስከ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅም

ሓሙስ ጥቅምት 19, 2019 46

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከዘጠና ዓመታት በላይ ታሪካዊ ጉዞ የሀገራችንን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ የተለየ ሚና የተወጣ አንጋፋ ተቋም ነው። ከታሪካዊ ጀግንነት ተነስቶ ወደ ዘመናዊ የመከላከያ አቅም የሚያደርገው ጉዞም የሀገራችንን ራስን የመቻል ራዕይ ከሚያሳዩ ዋና ዋና ጥረቶች መካከል ይጠቀሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “የአናብስቶቹ ሰማይ” በሚል መሪ ሐሳብ በተካሄደው የአየር ላይ ትርኢት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በብዙ ከፍታና ዝቅታዎች ውስጥ አልፎ የሀገራችንን ነጻነት እና ሉዓላዊነት በማስጠበቅ የነጻነት ምልክት ሆኖ መዝለቁን ገልጸዋል።

አየር ኃይሉ ሀገራችንን ለማጥቃት የሞከሩ ኃይሎችን በመመከት ታላቅ ታሪካዊ ዐሻራ ያሳረፈ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪካዊ ጥንካሬ በድል ታሪኮቹ ብቻ የሚለካ ሳይሆን፣ ከዘመኑ ጋር በመራመድ የቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል አቅሙን የማሳደግ ብቃቱም ጭምር ነው።

በዘመናዊ የመከላከያ ሥርዓት ውስጥ የአየር ኃይል ሚና እጅግ ወሳኝ ሲሆን፣ የአየር ክልልን ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የውጊያ ዝግጁነትን ማሳደግ እና የሀገርን ስትራቴጂያዊ ጥቅም ለማስከበር የሚያስፈልገውን አቅም ማጠናከር ዋነኛ ተግባሮቹ ናቸው።

በዚህም የአብራሪዎች ሙያዊ ብቃት፣ የቴክኒክ ባለሙያዎች ክህሎት፣ የዘመናዊ መሣሪያዎች አጠቃቀም እና የአየር መከላከያ ዝግጁነት የተቋሙን የመፈጸም አቅም የሚወስኑ መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው።

በተለይም የጄቶችንና የሄሊኮፕተሮችን ጥገና በራስ አቅም የመፈጸም፣ የቴክኖሎጂ እውቀትን የማሳደግና የሰው ኃይልን የማብቃት ችሎታ የውጭ ጥገኝነትን ለመቀነስና የሥራ ቀጣይነትን ለማረጋገጥ የላቀ ፋይዳ አለው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት አምስት ዓመታት አየር ኃይሉን በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል እና በዘመናዊ የውጊያ አቅም ለማጠናከር ሰፊ ሥራ መሠራቱን ገልጸው፣ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የአየር ኃይሉን አቅም በእጥፍ ለማሳደግ ግልጽ ዕቅድና በጀት በመያዝ ከዋና ዋና የቴክኖሎጂ አምራቾች ጋር በትብብር መሥራት መጀመሩን ተናግረዋል።

አየር ኃይሉን በ2030 ወደ አምስተኛ ትውልድ የውጊያ አቅም ለማሸጋገር ያለው ዕቅድም የዚሁ የማዘመን ጉዞ አካል ነው።

የመደመር መንግሥት ትኩረት የአየር ኃይሉን በመሣሪያ ማዘመን ብቻ ሳይሆን፣ ተቋሙ በራሱ አቅም የሚቆምበትን መሠረት ማጠናከርን ያካትታል። የሰው ኃይል ልማት፣ የጥገና አቅም፣ የቴክኖሎጂ እውቀት እና የሙያ ሥልጠና በተቀናጀ መልኩ ሲጎለብት ተቋሙ የተሰጡትን ተልዕኮዎች በብቃትና በቀጣይነት ለመፈጸም የሚኖረው አቅም ይጠናከራል።

በተጨማሪም ጠንካራና በቴክኖሎጂ የዘመነ የመከላከያ ተቋም መኖር ለሀገር ደኅንነትና ሉዓላዊነት እንዲሁም ለልማት የሚያስፈልገውን መረጋጋት ለማጠናከር ያግዛል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከወዳጅ ሀገራት ጋር በትብብር ለመሥራት ያላትን ቁርጠኝነት እንዲሁም ተስማምቶና ተባብሮ ማደግ ለሁሉም የሚጠቅም መንገድ መሆኑን በተደጋጋሚ አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያ የብሔራዊ ጥቅሟን፣ የሀገር ክብሯንና አንድነቷን እያስጠበቀች ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ እንደምትቀጥልም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪካዊነቱን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ ከሰው ኃይል ብቃት እና ራስን ከመቻል አቅም ጋር የማጣመር ጉዞ ላይ ይገኛል። ይህ ጉዞ የሰማይ ላይ ዘብ የሆነውን ተቋም አቅም ከማጠናከር ባሻገር የሀገራችንን ሉዓላዊነት፣ ደኅንነት እና ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ያለውን ዝግጁነት የሚያጎለብት ነው።

 በኢንቲሃድ አብራር

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: