ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሞስኮ እየተካሄደ በሚገኘው 3ኛው የሩሲያ–አፍሪካ ጉባኤ ላይ በመገኘት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንኑ አስመልክቶ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባሰፈሩት መልዕክት፣ በታሪካዊው መድረክ በሚተላለፉ ውሳኔዎች ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ የጋራ ቁርጠኝነት እና ትብብር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት ሀገራዊና አህጉራዊ መልዕክት፣ ኢትዮጵያ ለዘላቂ ብልጽግናዋ እና ለሁለንተናዊ ሀገራዊ ዕድገቷ መሠረት በሆኑ ሦስት ቁልፍ ምሰሶዎች ላይ ትኩረት አድርጋ በቁርጠኝነት እየሠራች እንደምትገኝ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያን የልማት አቅጣጫ በሚመለከት እንዳስገነዘቡት፣ ኢትዮጵያ የሚከተሉትን ዋና ዋና መስኮች የብልጽግናዋ መሠረት አድርጋ እያከናወነች ትገኛለች፦
1. የምግብ ዋስትና እና ምርታማነት፦ የግብርናው ዘርፍ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና አሠራር ተደግፎ ምርታማነቱ እንዲያድግ እና ሀገራዊ የምግብ ዋስትና በዘላቂነት እንዲረጋገጥ ማድረግ፤
2. አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት፦ ለኢንዱስትሪ፣ ለንግድ እና ለዜጎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚሆን ዘላቂ እና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት መሠረተ-ልማቶችን ማስፋፋት፤
3. የክህሎት እና የዕውቀት ሽግግር፦ የትምህርት፣ የቴክኖሎጂ እና የሙያ አቅምን በመገንባት ለወጣቱ ትውልድ የዕውቀትና የሥራ ዕድል ፈጠራን ማሳደግ ናቸው።
በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረ፣ በመከባበር እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የጸና ታሪካዊ ወዳጅነት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውስተዋል።
ይህንን ታሪካዊ አጋርነት ይበልጥ ወደ ላቀ እና ወደ ተጨባጭ ደረጃ ለማሸጋገር ከሩሲያ ጋር በጋራ በመሆን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት የሚያስችሉ ተግባራት በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየተከናወኑ እንደሚገኝ ይፋ አድርገዋል።
ይህ ስትራቴጂያዊ ትብብር የሀገራችንን የኃይል አማራጮች ከመጨመር እና ከማስፋት ባለፈ፣ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ በእጅጉ የሚያፋጥን እንዲሁም የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ትሥሥር ከምንጊዜውም በላይ የሚያጠናክር እንደሚሆን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: