በአዲስ አበባ ከተማ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል እና የምርት አቅርቦት እጥረትን ለመከላከል በተከናወኑ ሰፊ ሥራዎች ባለፉት 5 ዓመታት ብቻ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ወጪ የተደረገባቸው 5 ዘመናዊ እና ሁለገብ የገበያ ማዕከላት ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።
ከእነዚህም መካከል በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኙት የላፍቶ አንድ እና ሁለት የገበያ ማዕከላት ለሕብረተሰቡ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ረገድ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣታቸው ተገልጿል።
በማዕከሉ የሚገበያዩት ወ/ሮ ንጋት ገዛኸኝ እና ወ/ሮ እድላዊት ጌታቸው እንደተናገሩት፣ የገበያ ማዕከሉ እንደ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ድንች፣ ጤፍ እና ሌሎች መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን ከሌላው አካባቢ በጣም በቀነሰና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት ያስቻለ ነው።
በስፍራው ከሚሠሩ ነጋዴዎች መካከል አቶ አለነ ውበቴ እና አቶ ክብሩ ገብሬ በሰጡት አስተያየት፣ ማዕከሉ ሰፊ የመሸጫ ቦታ፣ የመኪና ማቆሚያ፣ ካፌዎች፣ የእህልና የአትክልት ተራዎችን ያካተተ በመሆኑ ሥራቸውን በስፋት ለማንቀሳቀስ እንደጠቀማቸው ገልጸዋል።
የማዕከሉ መከፈት አምራቾች ምርቶቻቸውን ያለ ደላላ ጣልቃ ገብነት በቀጥታ ለሕብረተሰቡ እንዲያቀርቡ እድል መፍጠሩንም አብራርተዋል።
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሰላማዊት ከበደ ገበያው የማኅበረሰቡን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ትልቅ አማራጭ መሆኑን ገልጸው፣ የምርት ዋጋውም ከ15 እስከ 30 በመቶ ቅናሽ ያለው በመሆኑ ገበያን ለማረጋጋት ትልቅ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው፣ የከተማዋ መግቢያ በሮች ላይ ያሉ 7 የግብይት ማዕከላት አምራቾች ምርታቸውን በቀጥታ የሚያቀርቡበት በመሆኑ የደላላዎችን ጣልቃ ገብነት ሙሉ በሙሉ ማስቀረታቸውን ገልጸዋል።
ይህም ዋጋን በማረጋጋት በርካታ ሆቴሎች እና ሕብረተሰቡ ያለምንም የምርት እጥረት እንዲስተናገዱ አድርጓል ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የገበያ ማዕከላቱን ተደራሽነት የበለጠ ለማስፋት የ5 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ አውጥቶ በየክፍለ ከተማው ለማዳረስ እንደሚሠራ ገልጸው፣ በዚህም በያዝነው ዓመት የጋራ የገበያ ማዕከል ደረጃውን ከፍ የማድረግ እንዲሁም በ2019 ደግሞ በመርካቶ አካባቢ አዲስ የገበያ ማዕከል የመጨመር ሥራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።
እነዚህ ዘመናዊ የግብይት ማዕከላት በአምራቹና በሸማቹ መካከል ቀጥተኛ ትሥሥር በመፍጠር፣ ደላላዎችን በማስወጣት እና ዋጋ እንዲቀንስ በማድረግ የዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቅለል እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመልክቷል።
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: