Search

የብሪክስ አዲስ የኢንዱስትሪ ትብብር ከልዩ ኢኮኖሚ ቀጣና እስከ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት

ሓሙስ ጥቅምት 19, 2019 44

የብሪክስ አባል ሀገራት በአሁኑ ወቅት የንግድ ልውውጦቻቸውን ከጫና ለመጠበቅ የሚያስችል ነፃና ገለልተኛ የክፍያ መሠረተ-ልማት በንቃት በመዘርጋት ላይ ናቸው።

በአህጉራዊ ደረጃ አፍሪካ ለብሪክስ ሀገራት ትልቅ ክፍት ገበያ እንዲሁም የቴክኖሎጂና የኢንዱስትሪ ምርቶች ማከፋፈያ ስትራቴጂካዊ ምኅዳር እየሆነች ነው።

አዲሶቹ የትብብር መሣሪያዎች ከፖለቲካዊ ውይይቶች አልፈው ወደ ተግባራዊ የንግድ ፕሮግራሞች በመሸጋገር ላይ ያሉ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣና ማህበር (Association of Special Economic Zones) እና አዲስ የሚቋቋመው የሰብል ልውውጥ (Grain Exchange) ሥርዓት ይገኙበታል።

እንዲሁም የአባል ሀገራቱ የኢንዱስትሪ አካላት በኢንዱስትሪዎች ዲጂታላይዜሽን እና ወደ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም በሚደረግ ሽግግር ዙሪያ የተለየ የትብብር መስመር እንዲቋቋም ጥሪ የቀረበ ሲሆን መንግሥታት የንግድ እንቅፋቶችን በማስወገድ ረገድ ድጋፍ ቢያደርጉም በመጨረሻ ግን የንግድ ማህበረሰቡ እና ባለሀብቶች ትክክለኛውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንደሚያከናውኑ ታምኖበታል።

በሌላ በኩል የብሪክስ ሀገራት በመሠረተ ልማት፣ በትራንስፖርት፣ በሎጂስቲክስ እና በኢነርጂ ዘርፎች የጋራ ፕሮጀክቶችን በጋራ መተግበር እንደሚገባቸው ግልጽ ነው።

በተለይም አዳዲስ የባቡር ቴክኖሎጂዎችን በጋራ ለማዳበር እና የትራንስፖርት ኮሪደሮችን ማስተሳሰር እንደሚገባ ጥሪ ቀርቧል።

ከዚህም በተጨማሪ በዘመናዊው የዲጂታል ዘመን እጅግ አሳሳቢ የሆነውን የሳይበር ደህንነት በበርካታ ዘርፎችና መተግበሪያዎች ውስጥ በጋራ ለመጠበቅ የሚያስችል ሰፊ ትብብር እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።

የወደፊቱን የንግድና የዲፕሎማሲ አጋርነት ለመጠበቅ ወጣቶችን በትክክለኛው አቅጣጫ ማስተማርና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ማሰልጠን እንደሚያስፈልግ፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ወጣቶች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እውቀት እየቀሰሙ መሆናቸው ተገልጿል።

ይህ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የኢንዱስትሪ ትብብር ማዕቀፍ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና የልማት ራዕይ ጋር በቀጥታ የሚጣጣም ሲሆን ሀገራችን ከባለፉት ዓመታት ጀምሮ የገነባቻቸው ዘመናዊ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና የማኑፋክቸሪንግ ማዕከላት የብሪክስ አባል ሀገራት ከሚያስተዋውቁት የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣና ትብብር እና ከእሴት ማሻሻያ ማዕቀፎች ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንድትሆን ትልቅ በር ይከፍታል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ ያላትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች መሠረተ-ልማት አቅም ከብሪክስ የንግድና የኢንቨስትመንት መሣሪያዎች ጋር በማቀናጀት የሀገር ውስጥ ምርቶችን ማሳደግ፣ የውጭ ንግድ አጋርነቶችን ማስፋፋት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማፋጠን የምትችልበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥራለች።

ከዚህም በተጨማሪ ከተጽዕኖ ነፃ በሆኑ የክፍያ ሥርዓቶች እና የሎጂስቲክስ አውታሮች በመጠቀም የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ምርቶች በቀጣናው እና በዓለም ገበያ ያላቸውን ተወዳዳሪነት በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚቻል መሆኑ እስተማማኝ እየሆነ መጥቷል።

በሰለሞን ገዳ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: