Search

የኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ጉዞ፡- ከኃይል አቅርቦት እስከ ሁለንተናዊ ብልጽግና

ሓሙስ ጥቅምት 19, 2019 57

ኢትዮጵያ ወደ ኒውክሌር ቴክኖሎጂ ልማት በይፋ መግባቷ ለዘመናት ከተጫናት የድህነት አዙሪት ለመውጣትና የኢኮኖሚ ነፃነቷን ለማረጋገጥ የወሰደችው እጅግ ስትራቴጂያዊ እርምጃ ነው።

ይህ ውሳኔ የዛሬን የኢነርጂ ፍላጎት ከማርካት ባለፈ፣ የአንድን መንግሥት ወይም ትውልድ ዕድሜ ተሻግሮ ለሚቀጥሉት ከ60 እስከ 100 ዓመታት የሀገራችንን ሁለንተናዊ የዕድገት አቅጣጫ የሚወስን መሠረታዊ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ነው።

ይህም ኢትዮጵያ የዕድገት ጉዞዋን ከተለምዷዊና ከአጭር ጊዜ የችግር ማስታገሻ መፍትሔዎች አውጥታ፣ በዘላቂ እና በሳይንሳዊ መሠረት ላይ እያቆመች መሆኑን ያሳያል።

የኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት ለረጅም ጊዜ በውሃ ኃይል ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ ለአየር ንብረት ለውጥ እና ለወቅቶች መፈራረቅ ተጋላጭ አድርጎት ቆይቷል።

በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደተገለጸው፣ እያንዳንዳቸው 1 ሺህ 200 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ ሁለት የኒውክሌር ዩኒቶችን ለመገንባት መታቀዱ ይህንን ስትራቴጂያዊ ክፍተት በዘላቂነት ይደፍናል።

ምንም እንኳን የኒውክሌር ማብላያ ግንባታ ከ10 እስከ 12 ዓመታትን የሚወስድና የመጀመሪያ ኢንቨስትመንት ወጪው ከፀሐይ፣ ከነፋስ እና ከውሃ ኃይል አንፃር ከፍተኛ ቢሆንም አንዴ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ የሚሰጠው ጥቅም እጅግ ከፍተኛ ነው።

የኒውክሌር ኃይል በወቅቶች መፈራረቅ ሳይዋዥቅ ዓመቱን ሙሉ በሙሉ አቅም በወጥነት ማመንጨት የሚችል በመሆኑ ሁለቱ ዩኒቶች በዓመት የሚያመርቱት አጠቃላይ የኢነርጂ መጠን ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዓመታዊ ምርት የሚልቅ ይሆናል።

ይህ አስተማማኝ የኃይል ምንጭ ደግሞ ለከባድ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የጀርባ አጥንት ከመሆኑም በላይ፣ ኢትዮጵያን በቀጣናው የኃይል ገበያ ውስጥ ወሳኝ ተዋናይ ያደርጋታል።

የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ትሩፋት በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ብቻ የሚገደብ አይደለም። ይልቁንም የዜጎችን የኑሮ ጥራት በቀጥታ የሚነካ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ መሣሪያ ነው።

በጤናው ዘርፍ በተለይም እንደ ካንሰር ያሉ ውስብስብ በሽታዎችን በጨረር ነጥሎ በማከምና በምርመራ መሣሪያዎች (እንደ X-ray እና MRI) አቅምን በማሳደግ ረገድ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው።

ይህም የዜጎችን ሕይወት ከመታደግና ለህክምና ወደ ውጭ የሚፈሰውን ምንዛሪ ከማስቀረት አልፎ ኢትዮጵያን የቀጣናው የጤና ቱሪዝም ማዕከል የማድረግ አቅም አለው።

በተመሳሳይ በግብርናው መስክ በሽታ አምጪ ተህዋስያንን በመቆጣጠር፣ የሰብል ዝርያዎችን በማሻሻልና ዘመናዊ ግብርናን በመተግበር የምግብ ዋስትናን በአጭር ጊዜ ለማረጋገጥ ያስችላል። ዘርፉ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ጋር ተሳስሮ መልማቱ ደግሞ፣ በሀራችን ውስጥ ከፍተኛ የዕውቀት ክምችትና ብቁ የሰው ኃይል እንዲፈጠር መሠረት ይጥላል።

ይህንን ታላቅ ውጥን ልዩ የሚያደርገው ከፖለቲካዊ መፈክርነት ወጥቶ ወደ ተጨባጭ ተቋማዊ ትግበራ መሸጋገሩ ነው። ራሱን የቻለ ተቋም በሕግ ተቋቁሞ፣ የሰው ኃይል ተመድቦለት እና ከ30 በላይ ቦታዎች በባለሙያዎች ተጠንተው በሂደት ወደ ሦስት ዕጩ ቦታዎች መጥበባቸው፣ ጉዳዩ በከፍተኛ ሳይንሳዊ ጥንቃቄና ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ጠብቆ እየተከናወነ መሆኑን ያረጋግጣል።

ከግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ ከተፈጥሮ ጋዝና ከማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታዎች ጎን ለጎን ይህ ፕሮጀክት መነደፉ፣ በታዳጊ ሀገራት ላይ የሚሰነዘረውን “ለእናንተ አይገባም፣ አቅሙም የላችሁም” የሚለውን የዝቅታ ትርክት በተግባር የሚሽር የሥነ-ልቦና ድል ጭምር ነው።

በአፍሪካ ሁለተኛዋ የሕዝብ ብዛት ባለቤት የሆነችውና 30 ሚሊዮን ወጣቶችን በትምህርት ገበታ ላይ የያዘችው ኢትዮጵያ፣ የዛሬ ውስን ሀብቷን ለዕለት ጉርስ ብቻ ሳታውል በኒውክሌር፣ በስፔስና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ ኢንቨስት ማድረጓ የሩቅ አሳቢነት መገለጫ ነው።

ቀደምት አባቶች እና እናቶች ለከርሞ የሚሆን ምርጥ ዘር ከጉርሳቸው ቀንሰው እንደሚያስቀምጡት ሁሉ የዛሬው ትውልድም ለነገው ትውልድ የማይነጥፍ የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ ጥሪት የማውረስ ታሪካዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።

ይህ ግዙፍ መሠረተ ልማት ከጠንካራ ተቋማዊ አሠራር እና ከላቀ የሥራ ባህል ጋር ተዳምሮ ሲተገበር፣ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 25 ዓመታት ውስጥ ድህነትን ታሪክ አድርጋ በአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን የጀመረችውን ጉዞ እውን እንደሚያደርገው ጥርጥር የለውም።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: