የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃዱ በባለሥልጣኑ ተሰርዞ የነበረው “ድምጺ ወያነ ትግራይ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን አገልግሎት” “ማእዶት ብሮድካስቲንግ አገልግሎት” በሚል አዲስ ስያሜ የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ መሰጠቱን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ይፋ አደረገ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 በተሰጠው ሥልጣን እና ኃላፊነት መሠረት ባደረገው ክትትል እና ቁጥጥር፣ ጣቢያው ቀደም ሲል ከመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ጋር የሚቃረኑ ይዘቶችን በሕገወጥ መንገድ ሲያሰራጭ በመገኘቱ የብሮድካስት ፈቃዱ ተሰርዞ እንደነበር ይታወሳል።
ቀደም ሲል ድምጺ ወያነ ትግራይ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን በሚል አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው ጣቢያ የጦርነት መሣሪያ ሆኖ በማገልገሉ ምክንያት ፈቃዱ መሰረዙን አስታውቋል።
አሁን ክልሉን የሚመራው ባለአደራ አስተዳደር የክልሉን ሰላም እና መረጋጋት በማረጋገጥ እንዲሁም የሕዝብ ድምፅ በመሆን አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የስያሜ ለውጥ በማድረግ፣ “ማእዶት ብሮድካስቲንግ አገልግሎት” በሚል አዲስ ስያሜ ተቀይሮ ፈቃድ እንዲሰጠው ጥያቄ ማቅረቡን ባለሥልጣኑ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቀረበለትን ጥያቄ ከመገናኛ ብዙኃን አዋጁ አንጻር በመመርመር ጥያቄው ተገቢነት ያለው መሆኑን በማመን የተቀበለው መሆኑን ገልጻል።
ስለሆነም ባለሥልጣኑ “ማእዶት ብሮድካስቲንግ አገልግሎት” በሚል አዲስ የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ የሰጠ መሆኑን ያሳወቀ ሲሆን፣ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለብሮድካስት አገልግሎቱ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪውን አስተላልፏል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: