Search

“በሩሲያ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው የወዳጅነት ባሕርይ እና የእርስ በርስ ግንኙነት ሁልጊዜም ትርጉም ያለው ነው”፦ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን

ሓሙስ ጥቅምት 19, 2019 29

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት፣ ሀገራቸው ለአፍሪካ በተለይም ለኢትዮጵያ ያላትን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንት ፑቲን በንግግራቸው ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በድጋሚ በጠቅላይ ሚኒስትርነት በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው የእንኳን ደስ አለዎ ብለዋል።

ኢትዮጵያ በ2019 በሶቺ እና በ2023 በሴንት ፒተርስበርግ በተካሄዱት የሩሲያ-አፍሪካ ስብሰባዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረጓን ያወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ አሁን በሞስኮ እየተካሄደ ባለው በሦስተኛው የሩሲያ-አፍሪካ የላቀ ጉባዔ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመገኘታቸው ምስጋና አቅርበዋል።

በሩሲያ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው የወዳጅነት ባሕርይ እና የእርስ በርስ ግንኙነት ሁልጊዜም ትርጉም ያለው እና ገንቢ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንት ፑቲን፣ መስከረም ወር በኒው ዴልሂ በተካሄደው የብሪክስ ጉባዔ ላይ ያደረጉትን ውይይት በማስታወስ፣ በውይይቶቹ በባለብዙ ወገን እና በሁለትዮሽ ትብብር ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ምክክር ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በ2026 ከጥር እስከ መስከረም ባለው የዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን እና መጠኑም ከ1.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን ገልጸዋል። ይህ አፈጻጸም በ2025 ሙሉ ዓመት አፈጻጸምን ከእጥፍ በላይ የሚበልጥ መሆኑን አብራርተዋል።

በኃይል፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ ትብብር፣ እስከ ጠፈር ሳይንስ፣ ጤና እና ትምህርት ባሉ የተለያዩ ዘርፎች በርካታ ሰፊ እና አዳዲስ ተስፋ ሰጪ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ሩሲያ እና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በጋራ አብረው መቆማቸውን የገለጹት ፑቲን፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በብሪክስ እና በሌሎችም ባለብዙ ወገን መድረኮች ውይይቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2027 የተመድ የአየር ንብረት ለውጥን ጉባኤን እንደምታስተናግድ ጠቁመው፣ ይህንን ትልቅ ዓለም አቀፍ መድረክ በስኬት እንድታጠናቅቅ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ሩሲያ አፍሪካን በአዲሱ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት ውስጥ አንዱ ቁልፍ ማዕከል እንድትሆን ሁልጊዜ እንደምትደግፍ ገልጸው፣ ለአፍሪካ ሀገራት የንግድ እና ኢኮኖሚ ትብብርን ማጠናከር፣ የምግብ እና የኃይል ዋስትናን ማረጋገጥ እና የጤና እንክብካቤን ማሳደግ ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አስምረውበታል።

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በሦስተኛ የሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ ዋና ዋና ሁነቶች ላይ እንደሚሳተፉ ገልጸው፣ በስብሰባው ማጠናቀቂያም የጉባዔውን መግለጫ እና ከ2027 እስከ 2029 የሚዘልቀውን አዲስ የሩሲያ-አፍሪካ አጋርነት መድረክ የትግበራ ዕቅድ እንደሚያጸድቁ አስታውቀዋል።

በዮናስ በድሉ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: