የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ በየመን ሰንዓ የአየር ጥቃት መፈጸሙን ገልጸዋል።
በጥቃቱም የየመን ፕሬዚዳንት ቤተመንግሥትን፣ የአሳር እና የሂዛዝ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን እና ለውትድር አገልግሎት ይውሉ ነበር የተባሉ የነዳጅ ማከማቻዎችን መምታቷን እስራኤል አስታውቃለች።
በእስራኤል የሚገኘው ካን ቲቪ እንደዘገበው በጥቃቱ 14 የጦር ጄቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ 40 የሚሆኑ ቦምቦችን መጣላቸውን ገልጿል።
በጥቃቱ በሁቲ ዓማጺያን ቁጥጥር ስር ያለው የየመን ፔትሮሊየም ኩባንያ የነዳጅ ማደያ ጣቢያ ላይ አደጋ ደርሷል። በአደጋው የሰው ሕይወት መጥፋቱን የቦታውን ምንጮች ጠቅሶ ዥንዋ ዘግቧል።
በሰንዓ ከተፈፀመው ጥቃት በኋላ የእሳት አደጋ ሰራተኞች እሳቱን ለማጥፋት እየሰሩ መሆኑን የየመን ሲቪል መከላከያ ባለስልጣን በመግለጫው አስታውቋል።
እስራኤል ከወራት በፊት በየመን ዋና አየር ማረፊያ ላይ ጥቃት መሰንዘሯ አይዘነጋም።
በጌትነት ተስፋማርያም