Search

የሽምቅ ውጊያ አይሳካም፦ ጄኔራል ሳሞራ የኑስ

ዓርብ ጥቅምት 20, 2019 101

የቀድሞው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ፣ በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ የፖለቲካ እና የፀጥታ ሁኔታ አስመልክቶ ከኢቢሲ የትግርኛ ቋንቋ ጋር ቃለ መጠይቅ አድርገዋል።

ጄኔራሉ በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ በትግራይ ሕዝብ ጥረት ክልሉ ዳግም የጦር ሜዳ እንዳይሆን መደረጉን ገልጸው፣ ከዚህ በኋላ ሕዝቡ አካባቢውን በመጠበቅ ትኩረቱን ወደ ሰላም፣ ትምህርት፣ ልማት እና መልሶ ማቋቋም ሥራዎች ላይ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

በክልሉ ባለፈው ጊዜ ለደረሰው ችግር “እንዲህ ነበርክ፣ እንዲያ ነበርክ” ከሚል መወቃቀስ በመውጣት፣ ትኩረትን ወደፊት በማድረግ ለጋራ ዓላማ መሥራት እንደሚያስፈልግ እና ያለፈውን ታሪክ ለታሪክ ጸሐፍት መተው እንደሚገባ መክረዋል።

በክልሉ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ሊቆሙ እንደሚገባ ያሳሰቡት ጄኔራል ሳሞራ፣ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሰላምን ይዞ የመጣ እና በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቅቡልነት ያገኘ መሆኑን አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ የሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን አመራሮች ሥልጣንን ብቻ አጀንዳ በማድረግ ስምምነቱን ከመጀመሪያው ጀምሮ ሲቃወሙ መቆየታቸውን፣ የትጥቅ መፍታት (DDR) ሂደት እንዳይፈጸም እንዲሁም ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ በማድረግ ክልሉ ሰላም እንዳያገኝ እንቅፋት መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

በቅርቡ የፌዴራል መንግሥት ያቋቋመውን የባለአደራ አስተዳደር እንደሚደግፉ የገለጹት ጄኔራሉ፣ የተልእኮ ባለቤቶች የሆኑት እነዚህ አካላት ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ ሁሉም ወገን ሊያግዛቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተለያዩ የትግራይ ክልል ከተሞች ሲገባ የሕዝቡ አቀባበል እና ድጋፍ የቡድኑን መሸነፍ በግልጽ እንደሚያሳይ እና ሕዝቡ ሰላም ፈላጊ መሆኑን በተግባር ያሳየበት መሆኑን አስረድተዋል። በዚህም የተነሣ የቡድኑ አመራሮች ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በሽምቅ ውጊያ ሊቀለብሱበት የሚችሉበት ሁኔታ የለም ነው ያሉት።

እንደ ጄኔራሉ ገለጻ፣ የሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን አመራሮች ከግብጽ እና ከሻዕቢያ ጋር በመተባበር የማያሸንፉትን የኢትዮጵያ መንግሥት ለማስፈራራት እና የውጭ ሎጅስቲክስ ለማስገባት ጥረቶች ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ሻዕቢያ ጠንካራ ኢትዮጵያ እንዳትኖር ስለሚፈልግ ትግራይን የጦር ሜዳ ለማድረግ ማቀዱን እና ግብጽም ኢትዮጵያ ያላት የተፈጥሮ ሀብት እንዳትጠቀም እንደምትፈልግ አብራርተዋል።

የቡድኑ አመራሮች “ከሕዝብ በፊት ፓርቲ መዳን አለበት” በሚል የተሳሳተ እሳቤ የውጭ ኃይሎችን ምክር በመስማት ሕዝቡን ለከፍተኛ ጉዳት የዳረጉ ቢሆንም፣ የትግራይ እና የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ድል ተቀዳጅተዋል ብለዋል።

አሁን ላይ የቡድኑ አመራሮች በጫካ ውስጥ ሆነው የሚያወጡት መግለጫ የጭንቅ እንጂ ሽንፈታቸውን ጠንቅቀው ያወቁ መሆኑን ጠቁመው፣ የሽምቅ ውጊያ ሊሳካ ስለማይችል እነዚህ ሰዎች ያለፉትን ስህተቶች አርመው እጃቸውን ለሰላም ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለሰላም እጃቸውን ካልሰጡ ግን ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ሽፍትነት ብቻ እንደሚሆን ጄኔራል ሳሞራ የኑስ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

 

በጌታቸው ዓለሙ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: