Search

የደረጃ "ሀ" የንግድ ትርፍ ግብር ማስታወቂያና መክፈያ ጊዜ ጥቅምት 30 ይጠናቀቃል፡- የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ

ዓርብ ጥቅምት 20, 2019 62

የ2018 የግብር ዘመን የደረጃ "ሀ" ዓመታዊ የንግድ ትርፍ ግብር ማሳወቂያ እና መክፈያ ጊዜ ጥቅምት 30 ቀን 2019 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ እንዳስታወቁት፣ የደረጃ "ለ" ግብር ከፋዮች የግብር ማሳወቂያ እና መክፈያ ጊዜ ከሐምሌ 1 እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ተጠናቆ አብዛኛዎቹ ግዴታቸውን ተወጥተዋል።  የደረጃ "ሀ" ግብር ከፋዮች ደግሞ ከሐምሌ 1 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ግብራቸውን እንዲያሳውቁ እና እንዲከፍሉ ሲጠበቅ ቆይቷል።

ቢሮው ከ2018 ዓ.ም ጀምሮ ወርሃዊ የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) እና የደመወዝ ግብር ማሳወቅ እና ክፍያ የመፈጸም ተግባርን ሙሉ በሙሉ በኦንላይን ማድረግ የጀመረ ሲሆን፣ ከ2019 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የደረጃ "ሀ"ግብር ከፋዮችን ዓመታዊ የንግድ ትርፍ ግብር የማሳወቅና የመክፈል ሂደት ሙሉ በሙሉ በበይነ-መረብ (ኦንላይን) እንዲከናወን አድርጓል።

በዚህም መሠረት ግብር ከፋዮች በአካል ወደ ቢሮ መምጣት ሳያስፈልጋቸው የሂሳብ መዝገቦቻቸውን በሲስተም አማካኝነት በመላክ እና ተጨማሪ አስፈላጊ ሰነዶችን በቃለ መሐላ በፈጸሙበት የኢሜይል አድራሻ በመላክ ሂደቱን ባሉበት ሆነው መከታተል ይችላሉ።

የኦዲት ሥራው ተከናውኖ የክፍያ ማዘዣ በሲስተሙ ሲደርሳቸው ክፍያቸውን በኦንላይን መፈጸም የሚችሉ ሲሆን፣ በአካል መምጣት የሚጠበቅባቸው በኦንላይን ለፈጸሙት ክፍያ ደረሰኝ ለማወራረድ ከካሸር ጋር ለመገናኘት ብቻ እንደሆነ ተጠቁሟል።

 

ይህ ዘመናዊ አሠራር ከዚህ ቀደም ይነሱ የነበሩ የግብር ከፋዮች እንግልት፣ ወረፋ እና ምልልስ በመቅረፍ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመፍታት ታስቦ የተዘረጋ በመሆኑ፣ ግዴታቸውን ያላጠናቀቁ የደረጃ "ሀ" ግብር ከፋዮች ከመጨረሻዎቹ ሰዓታት የሲስተም መጨናነቅ፣ ወረፋ እና ዘግይቶ ከሚመጣ ቅጣት ለመዳን ቀሪዎቹን ቀናት ተጠቅመው ግብራቸውን በኦንላይን እንዲያሳውቁና እንዲከፍሉ ቢሮው ጥሪ አቅርቧል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: