አስተማማኝ እና የማይቋረጥ የኃይል አቅርቦት ለኢንዱስትሪ መስፋፋት እና ለሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ወሳኝ ምሰሶ ነው። የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ተቋማዊና ቴክኒካዊ መሠረቶች መዘርጋታቸው፣ ሀገራችን ያላት የተትረፈረፈ ጸጋ ወደ ተጨባጭ የልማት ዕድል እየተቀየረ መሆኑን የሚያመላክት ነው።
የኒውክሌር ቴክኖሎጂ የኢኮኖሚ አቅምን ከማጎልበት ባለፈ፣ በዘመናዊው ዓለም ሳይንስና ፈጠራን በማበረታታት የግብርና፣ የጤና፣ የኢንዱስትሪ እና ተያያዥ ዘርፎችን የዕድገት ሽግግር በማፋጠን ከፍተኛ ሚና እየተወጣ ይገኛል።
ለምሳሌ ያህል በግብርናው ዘርፍ ምርጥ ዘርን በማፍራት እና ተባይን በመከላከል ረገድ የፈጠራና ምርምር ውጤቶችን በማቀናጀት ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ያስችላል። ከዚህም በላይ፣ ከአየር ብክለት የጸዳ እና አስተማማኝ የሆነ የኃይል አቅርቦት በመገንባት የሀገራችንን የኢንቨስትመንት አቅም ወደ ላቀ ከፍታ ለማሸጋገር ይረዳል።
ይህንን ግዙፍ ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክት ከግብ ለማድረስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሀገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር ብቁ የሰው ኃይል የማፍራት ስራዎችን በስፋት እያከናወኑ ይገኛሉ።
የኒውክሌር ፕሮግራም የዝግጅት፣ የግንባታ፣ የአወጋገድ እና የቁጥጥር ሂደቶች ጥብቅ ሙያዊ ብቃትን የሚጠይቁ በመሆናቸው፤ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ በሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሐ-ግብር ስልጠናዎች እየተሰጡ ሲሆን፣ በቀጣይም በመጀመሪያ ዲግሪ የኒውክሌር ሳይንስ ትምህርት ለመስጠት ዝግጅቶች እየተደረጉ ናቸው።
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለማስተማሪያነት የሚያገለግል የኒውክሌር ምርምር ሪአክተር ላቦራቶሪ ግንባታ በማጠናቀቅ የኒውክሌር ማዕከል አቋቁሞ ስራዎችን መጀመሩ ነው።
የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ቴክኖሎጂውን ለሰላማዊ ዓላማዎች ብቻ ለማዋል በበላይነት የሚቆጣጠር፣ ዘርፉን በብቃት ለመምራት የሚያስችሉ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ላይ መሆኑ፤ የሀገራችንን የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት በአስተማማኝ መሠረት ላይ የሚያቆም ነው።
የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሌር ልማት መርሐ-ግብር ስኬት የሚያሳየው፤ ሀገራት የረጅም ጊዜ የልማት ርዕያቸውን በሳይንሳዊ እውቀት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ መሰረት በማድረግ እውን ማድረግ እንደሚችሉ ነው።
የኃይል አማራጭ አስተማማኝነትን በማጎልበት የኢንዱስትሪ፣ የጤና እና የግብርና ምርታማነትን በአንድ ላይ ማሳደግ መቻል፤ የሀገርን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ማንሰራራት የሚያረጋግጥ የማይናወጥ ምሰሶ ነው።
በመሆኑም ተቋማዊ ትብብሮችን በማጠናከር፣ በሳይንስና ፈጠራ የተደገፈ የሰው ኃይል በማፍራት እና ዘርፉን በጠንካራ ፖሊሲዎች በመምራት የሚከናወነው የሰላማዊ ኒውክሌር ልማት ጉዞ፤ ለኢትዮጵያ ብልጽግና እና ለቀጣናዊ የኃይል ዋስትና ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።
#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: