በአዲስ አበባ ከተማ በነዳጅ ይሠሩ የነበሩ የመጀመሪያዎቹ 26 የከተማ አውቶብሶች ወደ ተፈጥሮ ጋዝ ተለውጠው ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ባለፉት ጥቂት ወራት የተፈጥሮ ጋዝ ምርትን ከሚመረትበት ስፍራ ወደ አዲስ አበባ የማጓጓዝ፣ የጋዝ ማደያዎችን የማዘጋጀት እና አውቶብሶቹን በራስ አቅም ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የመለወጥ ሰፊ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየቱንም ጠቁመዋል።
ይህ ታሪካዊ እርምጃ በነዳጅ ግዢ ላይ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ደረጃ የሚያስቀር ሲሆን የሕዝብ ትራንስፖርት የሥራ ማስኬጃ ወጪን በመቀነስ የዜጎችን የጉዞ ታሪፍ በግማሽ ያቃልላል።
በተጨማሪም ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ አቅም ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የመለወጡ ተግባር የቴክኖሎጂ ሽግግርን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
በነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት እና ሀገር ውስጥ የሚመረተውን የተፈጥሮ ጋዝ በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ 400 አዳዲስ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ አውቶብሶች በቅርቡ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ ታውቋል።
መንግሥት በምግብ፣ በቤት እና በትራንስፖርት ዘርፎች ላይ ተጨባጭ ሥራዎችን በማከናወን በዜጎች ሕይወት ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የጀመራቸው ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተገልጿል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: