የመጀመሪያዎቹ 26 የከተማ አውቶብሶች ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ ተለውጠው ዛሬ በሥራ ላይ መዋላቸው የተሰማቸውን ታላቅ ደስታ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፉት ጥቂት ወራት የተፈጥሮ ጋዝ ምርትን ከሚመረትበት ስፍራ ወደ አዲስ አበባ የማጓጓዝ፣ የጋዝ ማደያዎችን የማዘጋጀት እና የከተማ አውቶብሶችን ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የመለወጥ ሰፊ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውቀዋል።
ይህ ታሪካዊ እርምጃ በነዳጅ ግዢ ላይ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያስቀረው እና የሕዝብ ትራንስፖርት የሥራ ማስኬጃ ወጪን በመቀነስ የዜጎችን የጉዞ ታሪፍ በግማሽ እንደሚያቃልል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን በራስ አቅም ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የመለወጡ ተግባር የሀገር ውስጥ አቅምንና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጠቁመዋል።
በቀጣይም በነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት እና ሀገር ውስጥ እያመረቱ ያለውን የተፈጥሮ ጋዝ በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ 400 አዳዲስ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሠሩ አውቶብሶች በቅርቡ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ ገልጸዋል።
በምግብ፣ በቤት እና በትራንስፖርት ዘርፎች ላይ ተጨባጭ ሥራዎችን በማከናወን በዜጎች ሕይወት ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የተጀመሩት አበረታች ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: