በአዲስ አበባ ከተማ የሚሰጠውን የትራንስፖርት አገልግሎት በፍጥነት ወደ ተፈጥሮ ጋዝ ተጠቃሚነት ለማሸጋገር 400 አዳዲስ በጋዝ የሚሠሩ አውቶብሶች መታዘዛቸውን እና በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ የነበሩትን አውቶብሶች በሀገር ውስጥ በኮንቨርሽን መቀየሩ ረዘም ያለ ጊዜ ስለሚወስድ እና በምንፈልገው ፍጥነት ለመጓዝ ስለማያስችል እነዚህ 400 አዳዲስ በጋዝ የሚሠሩ አውቶብሶች እንዲታዘዙ ተደርጓል።
እነዚህ አውቶብሶች ገብተው አገልግሎት ሲጀምሩ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ የሚሰጠውን የአንበሳ ባስ አገልግሎት 34 በመቶ የሚሸፍኑ ይሆናል።
የመንግሥትን የረጅም ጊዜ ዕቅድ እና ቀጣይ እርምጃዎችን ሲያብራሩም፣ አዳዲሶቹ አውቶብሶች እስኪገቡ ድረስ እና ከዚያም በኋላ የነበሩትን አውቶብሶች ሞተር ወደ ጋዝ የመቀየሩ ሥራ በተፋጠነ መልኩ ይከናወናል ብለዋል።
በሦስት ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነዳጅ የሚጠቀሙ የሕዝብ አውቶብሶችን ሙሉ በሙሉ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ ተጠቃሚነት የመቀየር ግብ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል።
ይህ ስትራቴጂያዊ ውሳኔ የከተማዋን የትራንስፖርት መጨናነቅ ከመቅረፉ ባሻገር ዘመናዊ እና ቀልጣፋ የአገልግሎት ሥርዓት ለመዘርጋት ትልቅ መሠረት እንደሚጥል ተመላክቷል።
#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: