Search

የኢትዮጵያ የመከላከያ ልዕልና ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች

ዓርብ ጥቅምት 20, 2019 46

የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል እና በአደረጃጀት ታግዞ አቅሙን ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሯል። ተቋሙ ታሪካዊ የጀግንነት ውርሱን ከዲጂታል ዘመን የጦር ስትራቴጂ ጋር በማጣመር የባሕር፣ የየብስ እና የሰማይ ላይ አስተማማኝ የበላይነትን ተጎናጽፏል።

በተለይም ዘመናዊ የጦር አውሮፕላኖችን፣ የሚሳኤል መከላከያዎችን እና የድሮን ቴክኖሎጂዎችን በሀገር ውስጥ መሐንዲሶች የመጠገንና የማሻሻል ብቃቱ፣ የሠራዊታችንን የውጊያ ዝግጁነት በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጎታል።

ይህ የተቀናጀ እና ዘመናዊ መዋቅር ማንኛውንም የውስጥ እና የውጭ የደህንነት ስጋት አስቀድሞ መግታት የሚችልበትን ብቃት ጨምሮለታል፤ ይህም ሀገራችን ብሔራዊ ጥቅሟን እና ሉዓላዊነቷን በማይናወጥ መሰረት ላይ እንድታቆም አስችሏታል።

በሌላ በኩል የአንድ ሀገር ወታደራዊ ጽኑ ዝግጅት እና የቴክኖሎጂ አቅም ከጦር ሜዳ ባለፈ በዲፕሎማሲ እና በኢኮኖሚ ልማት ላይ ቀጥተኛ እና በጎ ተጽዕኖ ይፈጥራል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ አየር ክልሏን በማይበገር የብረት አጥር ማዋቀሯ እና የኃይል ሚዛኑን በባለቤትነት መቆጣጠሯ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞችን አስገኝቶላታል።

ለአብነትም ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ያላት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ውጤት የሆኑትን የሱ-35 (Su-35) ተዋጊ ጄቶች እና የኤስ-400 (S-400) ሲስተም መረከቧ፣ ሀገራችን በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ የፈጠረችውን ከፍተኛ ተጽዕኖ በጉልህ ያሳያል።

ከዚህ ባለፈም በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባሕር ቀጣና የኃያላኑ ጣልቃገብነት ባየለበት ወቅት ኢትዮጵያ ጠንካራ የመከላከያ አቅም መገንባቷ፣ የሌሎችን ጫና በመቋቋም ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ትልቅ የዲፕሎማሲ መሣሪያ ሆኖላታል፤ ይህ አቅም ለአካባቢው ደህንነት ዋስትና በመሆንም የቀጣናው መሪነቷን ያጠናክረዋል።

በተጨማሪም አየር ክልሉ ሙሉ በሙሉ የተጠበቀ መሆኑ እና የትኛውንም ስጋት በቅጽበት ማክሸፍ መቻሉ ለኢኮኖሚው እንቅስቃሴ አስተማማኝ መሰረት ይጥላል፤ ለኢንቨስትመንትም ዋስትና ይሰጣል። በዚህም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር ያደርጋል።

ደህንነቱ የተጠበቀ የአየር ክልል የንግድ በረራዎች ያለምንም ማቋረጥ እንዲቀጥሉ በማድረግ የቱሪዝም እና የንግድ ገቢዎችን ከፍ ያደርጋል፤ የሀገራችንን ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ከማንኛውም ውጫዊ ስጋት በመጠበቅም የኢኮኖሚ ቀጣይነትን ያረጋግጣል።

ባጠቃላይ የኢትዮጵያ የሰማይ ላይ ልዕልና እና የጸና መከላከያ ግንባታ ከወታደራዊ ጥንካሬ ባሻገር የዲፕሎማሲ አቅም ማላቂያ እና የኢኮኖሚ ልማት ዋስትና ነው።

#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

 

በዓይናለም ሃድራ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: