Search

የኢትዮጵያ እና የሩስያ ስትራቴጂያዊ አጋርነት፡ ከታሪካዊ ወዳጅነት ወደ ሁለንተናዊ የትብብር ከፍታ

ሓሙስ ጥቅምት 19, 2019 160

እ.ኤ.አ በ1898 በይፋ የተጀመረው የኢትዮጵያ እና የሩስያ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የዘመናት ፈተናዎችን በጽናት በመሻገር አሁን ላይ ወደ ሁለንተናዊ ስትራቴጂያዊ አጋርነት አድጓል። 

ኢትዮጵያ እና ሩስያ የአውሮፓን የቅኝ ግዛት ፍላጎት በመመከት ሉዓላዊነትን የማስከበር እንዲሁም ታሪካዊ የእምነት እና የባህል ቁርኝትን የመጠበቅ የጋራ መሠረት አላቸው።

 

ሩስያ በዓድዋ ድል ማግስት በጦርነቱ የቆሰሉትን ለማከም የሕክምና ቡድን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ፣ የጣሊያንን የቅኝ ግዛት ፍላጎት በሊግ ኦፍ ኔሽንስ በጽኑ በማውገዝ እንዲሁም የዚያድ ባሬን ወረራ ኢትዮጵያ በድል እንድታጠናቅቅ ድጋፍ በማድረግ ከሀገራችን ጎን የቆመች የቁርጥ ቀን ወዳጅ መሆኗን በተግባር አስመስክራለች። 

በታሪክ ምዕራፎች የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የትምህርት ዕድል በመስጠት እና የተለያዩ የኢንዱስትሪና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት ያጠናከረችው ይህ የቆየ ወዳጅነት፣ ዛሬ ላይ ከመከላከያና ንግድ ባሻገር በኒውክሌር ኃይል፣ በግብርና፣ በዲጂታል ንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በሜጋ ፕሮጀክቶች ልማት ላይ ወደተመሠረተ የላቀ የጋራ ተጠቃሚነት ተሸጋግሯል። 

ኢትዮጵያ በሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ድጋፍ የብሪክስ (BRICS) ሙሉ አባል መሆኗም የሁለቱን ሀገራት ስትራቴጂያዊ አጋርነት ይበልጥ በማጠናከር በዓለም አቀፍ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ምህዳር ከባለ ነጠላ-ዋልታ ወደ ባለ ብዙ-ዋልታ የሚደረገውን የኃይል ሚዛን ሽግግር ለማፋጠን ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

 

በሞስኮ እየተካሄደ በሚገኘው 3ኛው የሩስያ-አፍሪካ ጉባኤ እየተሳተፉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ከፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በኢትዮጵያና በሩስያ መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ፍሬያማ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። 

ከሩስያ መንግሥት ጋር ቀደም ሲል በተደረሰው ስምምነት መሠረትም ኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹን 12 የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄቶች እንዲሁም 4 የኤስ-400 የአየር መከላከያ ሥርዓት ባትሪዎችን ተረክባለች። 

እነዚህን ዘመናዊ የጦር ጄቶች በመታጠቅ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚዋ ስትሆን፣ ይህም የሀገራችንን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም ይበልጥ እንደሚያስከብር እንዲሁም ቀጣናዊ የጋራ ደህንነትን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጉዞ በልበ ሙሉነት እንድትቀጥል ትልቅ አቅም እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል። 

በተጨማሪም ሩስያ የኢትዮጵያን የአየር መከላከያና የአቪዬሽን ዘርፍ፣ በተለይም የኤም.አይ ሄሊኮፕተሮችን (Mi-24 እና Mi-17) እንዲሁም የቲ-72 (T-72) ታንኮችን የማዘመን ሥራ እያከናወነች ነው። ከዚህም ባሻገር ዘመናዊ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖችን) ለማቅረብ እና በቢሾፍቱ የሚገኘውን የታጠቁ ተሽከርካሪዎች ማምረቻና ጥገና ማዕከልን ለማዘመን በአጋርነት እየሠራች ነው።

 

በኢነርጂው ዘርፍ በተለይ በኒውክሌር ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድም ሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ። የሩስያው የኒውክሌር ኃይል ግዙፍ ኩባንያ ሮሳቶም (Rosatom) ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በመተባበር የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል። 

በዚሁ መሠረት እ.ኤ.አ እስከ 2032 እና 2034 ባለው ጊዜ እያንዳንዳቸው 1 ሺህ 200 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችሉ ሁለት የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎችን ለመገንባት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። 

በተጨማሪም ለሕክምና፣ ለግብርና እና ለኢንዱስትሪ አገልግሎት የሚውል የኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል በኢትዮጵያ ለማቋቋም ጥናት እየተደረገ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የሩስያው ሩሳል ኩባንያ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ግዙፍ የአልሙኒየም ማቅለጫ ፋብሪካ ለመገንባት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል። 

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ልውውጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሦስት እጥፍ በማደግ እ.ኤ.አ በ2025 435 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል። 

ኢትዮጵያ በዋናነት ቡና እና የደረቁ የጓሮ አትክልቶችን ወደ ሩስያ ገበያ ስትልክ፣ ሩስያ በአንፃሩ ልዩ ልዩ የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ምርቶችን ለኢትዮጵያ ታቀርባለች። 

በግብርናው ዘርፍ ሩስያ የኢትዮጵያን 28 በመቶ የማዳበሪያ ፍላጎት ከመሸፈኗ ባሻገር፣ ድርቅን መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን በባዮ-ኢንጂነሪንግ ቴክኖሎጂ ለማቅረብ እና የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት እየሠራች ትገኛለች። 

በዲጂታል ንግድና የሎጂስቲክስ ትስስር በኩልም የሩስያው ዋይልድ ቤሪስ ኤንድ ሩስ ኩባንያ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጋር በመተባበር የኤሌክትሮኒክስ ንግድ እና የሎጂስቲክስ መሠረተ ልማቶችን ለማስፋፋት ተስማምተዋል። 

በተጨማሪም የሩስያ አምራቾች የቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንን መነሻ አድርገው የኢትዮጵያን አቅም በመጠቀም ወደ አፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ገበያ ለመግባት ሰፊ ፍላጎት አሳይተዋል። 

በአጠቃላይ ከ128 ዓመታት በላይ የዘለቀው የኢትዮጵያና የሩስያ ታሪካዊ ወዳጅነት ዛሬ ላይ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በመመስረት የቀጣናውን እና የዓለምን የኃይል ሚዛን ወደሚያስጠብቅ ዘመናዊ የኢኮኖሚ፣ የቴክኖሎጂ እና የደህንነት ስትራቴጂያዊ አጋርነት ደረጃ ደርሷል። 

በላሉ ኢታላ 

#Ethiopia #EthioRussiaRelations #StrategicPartnership # RussiaAfricaSummit #BRICS #EBC

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: