ኢትዮጵያ በአፍሪካ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አብዮት ማዕከል እንድትሆን ያስቻላት ታሪካዊ ጉዞ፣ ሀገራችንን የዜሮ-በካይ ጋዝ ሽግግር የዲፕሎማሲ ማዕከል አድርጓታል።
የብዙኃን ትራንስፖርትን በኤሌክትሪክ በመተካት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መሙያዎችን በማስፋፋት እና በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ማሳደግ ላይ ያተኮረው ይህ አጠቃላይ ስትራቴጂ፣ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ገጽታ ሙሉ በሙሉ እየቀየረ ይገኛል።
ኢትዮጵያ የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ የያዘቻቸውን ብሔራዊ ግቦች ለማሳካት የትራንስፖርት ዘርፉ ትልቅ ድርሻ እንዳለው በማመን፣ ለነዳጅ ግዢ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማዳን በሀገር ውስጥ በሚመረት ንጹህና ታዳሽ ኃይል ለመጠቀም ቆርጣ ተነስታለች።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና የማክሮ ኢኮኖሚ ጫናን ለመቀነስ ሲባል፣ ኢትዮጵያ በጥር ወር 2016 ዓ.ም በነዳጅ የሚሠሩ የቤት አውቶሞቢሎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትን በማገድ በዓለም የመጀመሪያዋ ሀገር መሆኗ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የታዳሸ ኢነርጂ ዘርፍ ሽግግር ከህልም ወደ እውን የተቀየረበት ታሪካዊ የታዳሽ ኃይል አብዮት በትክክለኛ ፖሊሲ እየተመራ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል። ላለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ንፁህ ኢነርጂን ከመመኘት አልፋ ወደ ታዳሽ ኃይል ማማነት እያደረገች ያለው ተግባራዊ ጉዞ፣ የሀገራችንን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ገጽታ በመሰረታዊነት እየቀየረ ነው።
ይህንን የንፁህ ኢነርጂ ስትራቴጂ በተግባር ለመተርጎም የተወሰዱት የሜጋ ፕሮጀክቶች እርምጃዎች የሀገራችንን አቅምና ጽናት በፈተና ውስጥ ያሳለፉ ግዙፍ ምዕራፎች ናቸው። ከውጭ ብድር ነፃ በሆነ የሀገር ውስጥ አቅም እና ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን በመቋቋም የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንዲሁም በግንባታ ላይ ያለው የኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ የዚህ ታሪካዊ ሽግግር መሠረቶች ናቸው።
በተጓዳኝም የአይሻ እና የአሰላ የንፋስ ኃይል ፕሮጀክቶች፣ የቱሉ ሞዬ እና ኮርቤቲ የጂኦተርማል ማመንጫዎች፣ እንዲሁም የተለያዩ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ጅምሮች ሀገራችንን በዓለም ላይ ካሉ እጅግ ጥቂት ንፁህ ኢነርጂ አምራች ሀገራት ተርታ አሰልፈዋታል።
እነዚህን ግዙፍ የኃይል ማመንጫዎች ከአየር ንብረት መዛባትና ከዝናብ መዋዠቅ ለመጠበቅ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ማልማት፣ ለግድቦቹ ዋነኛ ስጋት የሆነውን የደለል ሙሌት በመከላከል የኃይል ማመንጫዎቹን የአገልግሎት ዘመን አራዝሟል።
ይህ ሥነ-ምህዳራዊ ጥበቃ የካርቦን ልቀትን ከመምጠጥ ባለፈ የውኃ ሀብትን ዘላቂነት በማረጋገጥ የኢነርጂ ዘርፉን ደህንነት በእጅጉ አጠናክሯል። በዚህም በውኃ፣ በንፋስ፣ በጂኦተርማል እና በፀሐይ ኃይል አጠቃቀም ሀገራችን የደረሰችበት ደረጃ ለቀጣናው እና ለአፍሪካ ትልቅ ምሳሌ ሆኗል።
የዚህ ሁሉን አቀፍ የታዳሽ ኢነርጂ ክምችትና የሥነ-ምህዳር ጥበቃ ስኬት በጉልህ የሚንፀባረቀው ደግሞ በአረንጓዴ ትራንስፖርት ፖሊሲ ነው። የመደመር መንግሥት በነዳጅ የሚሰሩ የቤት አውቶሞቢሎች ላይ ያሳለፈው ቆራጥ ውሳኔ፣ ትራንስፖርቱን ከካርቦን ነፃ ለማድረግ የተጀመረ ታሪካዊ እርምጃ ነው።
ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለነዳጅ ግዢ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ታወጣለች። ይህንን ውድ የነዳጅ ወጪ በሀገር ውስጥ ታዳሽ ኃይል ለመተካት፣ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መሸጋገር አማራጭ የሌለው የመፍትሔ እርምጃ ሆኗል። ይህ ፖሊሲ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የነዳጅ ወጪን ከማዳን ባሻገር፣ በነዳጅ ላይ የተመሰረተውን የኢንዱስትሪ ሽግግር በማለፍ በቀጥታ ወደ ድህረ-ካርቦን አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለማምራት የሚያስችል ነው።
የአረንጓዴ ትራንስፖርት ሥርዓትን መገንባት የቅንጦት ሳይሆን ከመሰረታዊ ፍላጎቶቻችን አንዱ ሲሆን፣ የትራንስፖርት ዘርፉን ከነዳጅ ጥገኝነት በማላቀቅ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ እና ወደ ንፁህ የኃይል ምንጭ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ የተነደፈው ስትራቴጂ ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ያላትን ቁርጠኝነት በግልጽ ያሳያል።
በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማጠናከር የሚያስችል የመሠረተ ልማት ግንባታ እየተስፋፋ ይገኛል። የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር፣ አዳዲስ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች፣ እንዲሁም በከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች እግረኛ እና የብስክሌት መንገዶችን በማካተት ካርቦን-አልባ የትራንስፖርት አማራጮችን እያበረታቱ ናቸው።
በዓለም አቀፉ ትራንስፖርት ልማት ፖሊሲ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬክተር ክሪስ ኮስትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ አካላት የኢትዮጵያን የግሪን ሞቢሊቲ ተሞክሮ አድንቀዋል። አዲስ አበባ ያስተናገደችው የአፍሪካ ኢ-ሞቢሊቲ ሳምንት እና በቀጣይ የሚጠበቀው የኖርዲክ-አፍሪካ ኢቪ ጉባኤ ኢትዮጵያን ለአፍሪካ የዜሮ-በካይ ጋዝ ሽግግር የዲፕሎማሲ ማዕከል አድርገዋታል።
በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማሳደግም ሙሉ በሙሉ ያልተገጣጠሙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን አምጥተው ሀገር ውስጥ ለሚገጣጥሙ አምራቾች ከፍተኛ የታክስ ማሻሻያና ማበረታቻ ተሰጥቷል።
በአጠቃላይ በጠንካራ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ በኢነርጂ ዘርፍ መነቃቃት እና በፖሊሲ ቁርጠኝነት ታግዞ ኢትዮጵያ የጀመረችው አረንጓዴ የትራንስፖርት አብዮት ዓለም አቀፍ አርአያነት ያለው እና ለቀጣይ ትውልድ የበለፀገች ሀገርን ለማስረከብ የሚያግዝ ምዕራፍ ነው።
በላሉ ኢታላ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: