Search

ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል የዓለም አቀፍ የተጓዦች ትሥሥር ቴክኖሎጂን ልትተገብር ነው፡- ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል

ቅዳሜ ጥቅምት 21, 2019 133

ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከልና ወንጀለኞች ተላልፈው እንዲሰጡ ለማድረግ ዓለም አቀፍ የተጓዦች ትሥሥር ቴክኖሎጂን ልትተገብር መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

በኢንተርፖል የለማው ይኼው ዓለም አቀፍ የተጓዦች ትሥሥር ቴክኖሎጂ ሥርዓት ሽብርተኝነትና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ሠርተው የተደበቁ ወንጀለኞች ህግን ተከትሎ ለአባል ሀገራት ተላልፈው እንዲሰጡ ማድረግ የሚያስችል ነው።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በቀጣናው በገነባው ጠንካራ የወንጀል መከላከል አቅምና ከኢንተርፖል ጋር ባለው የተቀናጀ ትብብር ለአባል ሀገራት የሕግ አስከባሪዎች ደረጃውን የጠበቀና ጥራት ያለው ሥልጠና በመስጠት ከሚታወቀው የኢንተርፖል ግሎባል አካዳሚ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እንደገለጹት፣ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች በቴክኖሎጂ የታገዙና ውስብስብ የሆኑበት ዘመን ተፈጥሯል።

እነዚህን ውስብስብ ዓለም አቀፋዊ ወንጀሎች ለመቆጣጠርና ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህም ኢንተርፖል ድንበር ዘለል ወንጀሎችን መከላከልና ወንጀል ሠርተው የተደበቁ አካላት ተላልፈው የሚሰጡበት ዓለም አቀፍ የተጓዦች ትሥሥር ቴክኖሎጂ ሥርዓት ማልማቱን ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው በሽብርተኝነት ወይም በሌላ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል የሚፈለጉ አካላትን በየትኛውም ሀገር ላይ በቀላሉ ለመቆጣጠር ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀለኞችን ባሉበት ቦታ ለመያዝ ከኢሚግሬሽንና አየር መንገድ ጋር በሚኖረው ቅንጅት ላይ እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው ወንጀለኛ የትም ቦታ መደበቅ እንዳይችል የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፣ ገቢራዊ ለማድረግ በሂደት ላይ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እንዲጠናከር በማድረጋቸው ከኢንተርፖል ጋር ጥብቅ ትብብር መፍጠር ማስቻሉን አመላክተዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ከኢንተርፖል ጋር በሠራው የተቀናጀ ዘመቻ አንድ ወንጀለኛ ተይዞ ለኢትዮጵያ ተላልፎ እንዲሰጥና ለህግ እንዲቀርብ ተደርጓል ያሉት ጠቅላይ አዛዡ፣ ኢትዮጵያም በተለያዩ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች የሚፈለጉ አካላትን ህግና ሥርዓት በመከተል ለሀገራት ተላልፈው እንዲሰጡ ማድረጓን ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው በቀን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በመከታተል ወንጀለኞችን በቀላሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በደረቅ ወደብና በሌሎች የትራንስፖርት ዘርፎች የሚስተዋሉ የሽብር እንቅስቃሴዎችና ወንጀሎችን ተከታትሎ መያዝ እንደሚያስችልና በቅርቡም ተግባራዊ እንደሚደረግ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: