Search

የዓለም ገበያ ጫናን መቋቋም፡ ተኪ ምርቶችን ማስፋት

ቅዳሜ ጥቅምት 21, 2019 138

በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከሰቱ ያሉ ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች፣ የሎጂስቲክስ መስመሮች መስተጓጎልና የምርት ማነቆዎች በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ ይገኛሉ።

በተለይም የነዳጅ፣ የቅባት እህሎችና የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃዎች ዋጋ መናር በገቢ ምርቶች ላይ ጥገኛ በሆኑ ሀገራት ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና እየፈጠረ ነው።

የዓለም አቀፍ የንግድና የሎጂስቲክስ መስመሮች መስተጓጎል፣ በሀገራችንም የምርት ዋጋ እንዲጨምርና ዜጎች በኑሮ ጫና እንዲፈተኑ ምክንያት መሆኑን የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ ግርማ ተሾመ (ዶ/ር) ይገልጻሉ።

በተለይም ሀገራችን ከውጭ የምታስገባቸው እንደ ማዳበሪያና የሕክምና ግብዓቶች ያሉ ምርቶች ዋጋ በዓለም ገበያ በሚከሰት መዛባት ሲጨምር፣ ይህ በቀጥታ ወደ ሀገር ውስጥ ገበያ በመተላለፍ በተጠቃሚዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥር አብራርተዋል።

ይህን መሰሉን የውጭ ተጽዕኖ በዘላቂነት ለመቋቋምና ከጥገኝነት ለመላቀቅ የሀገር ውስጥ ምርትን እና ምርታማነትን ማሳደግ እና ማስፋት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ በመነሳት የመደመር መንግሥት ሀገራዊ አቅምን የሚገነቡ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይም ባለፉት ዓመታት በስንዴ ልማት ላይ የተሠራው ሥራ የምግብ ዋጋ እንዲረጋጋና ሀገራችን ከጥገኝነት እንድትላቀቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ፣ በ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማጠናከር ከውጭ የሚገቡ በርካታ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት መተካት መቻሉን አንስተዋል።

እነዚህ ሥራዎች የውጭ ምንዛሬን ከማዳን ባለፈ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የዜጎችን ገቢ በማሳደግና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው አስረድተዋል።

በሌላ በኩል አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን የመግዛት አቅም ለመደገፍ የማኅበራዊ ደኅንነት አሠራር መተግበሩን አንስተው፣ የከተማና የገጠር ሴፍቲኔት መርሐ ግብርን በአብነት ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ምርታማነትን ማሳደግ፣ የግብርናውን ዘርፍ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መደገፍ፣ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ማሳደግና ቀጥተኛ የገበያ ትስስር መፍጠር የመደመር መንግሥት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው።

በተለይም የምግብ ምርትን ማሳደግ፣ በቂ ምግብ ማሰራጨትና የአቅርቦት አድማስን ማስፋት እንዲሁም የቤት ኪራይ ዋጋን ማረጋጋት የዜጎችን የኑሮ ውድነት ጫና ለማቃለል ወሳኝ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስገንዝበዋል።

በጥቅሉ የዓለም ገበያ መዛባት የሚያስከትለውን የዋጋ ንረት ለመቋቋም የተጀመረውን የሀገር ውስጥ ምርትን የማሳደግ እና የዜጎችን የመግዛት አቅም የመደገፍ አሠራርን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል።

በኢንቲሃድ አብራር

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: