የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚረጋገጠው በወረቀት ላይ በሚቀረጹ ራዕዮች ብቻ ሳይሆን ያን ራዕይ ወደ መሬት አውርዶ መፈጸም በሚያስችል ብቃት፣ ቁርጠኝነት እና ጽናት በታነጸ አመራር ነው።
በዚህ ረገድ የመደመር መንግሥት አመራሮች በታሪካዊው የሁርሶ ወታደራዊ ማሠልጠኛ በመገኘት እየወሰዱት ያለው ጥልቅ ወታደራዊ ሥልጠና የመደመር ሥልጣኔን እውን የማድረግ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።
የመደመር ፍልስፍና መሠረቱ ከፋፍሎ ማየት ሳይሆን፣ ሁሉንም ዘርፎች አስተሳስሮ ለአንድ የገነነ ሀገራዊ ግብ ማሰለፍ ነው። የመደመር ሥልጣኔ የሰውን አዕምሮ፣ የሀገርን ሀብት እና የሞራል ልዕልና አስተባብሮ አዲስ ታሪክ መሥራት ማለት ነው።
አመራርነት በምቾት ዞን ውስጥ ተወስኖ የሚከናወን ሳይሆን የሕዝብን ውጣ ውረድ በመረዳት ፈተናዎችን በተጨባጭ ተሻግሮ የማሳየት እና የውሳኔ ሰጪነት ጽናትን የመጨበጥ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው።
አመራሮቹ በጽኑ ወታደራዊ ዲሲፕሊን ሠልጥነው አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ፈተናዎችን መሻገራቸው፣ የሀገርን አደራ በቁርጠኝነት ለመወጣት የሚያስችል አዲስ የሥራ ባህል ለመላበስ ያስችላቸዋል።
በሌላ መልኩ ሥልጠናው አመራሮቹ የዘመኑን ተለዋዋጭ ጂኦፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጫናዎች በመቋቋም ተልዕኳቸውን በውጤታማነት መፈጸም እንዲችሉ የሚያበቃቸው ወሳኝ ስትራቴጂያዊ እርምጃ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተፈጠሩ ያሉ ውስብስብ የጂኦፖለቲካ ፉክክሮች እና አህጉራዊ ተግዳሮቶች እስከዛሬ በመጣንበት መደበኛ የአስተዳደር ዘይቤ ብቻ የምንወጣቸው አይደሉም።
በመሆኑም የመደመር መንግሥት አመራሮች በወታደራዊ ሳይንስ ዲሲፕሊን መታነጻቸው ተቋማት ከቀውስ ነጻ እንዲሆኑ፣ ለሕዝብ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ እና የሀገርን የልማትና የሰላም ጉዞ በውጤታማነት እንዲመሩ የላቀ ፋይዳ አለው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉትም፣ “ሕዝብን ለዓላማና ለተግባር ማነጽ፤ ለሕዝብ የገባነውን ቃል በሚገባ አከናውኖ መጨረስ፤ ከታች እስከ ላይ ያለውን መዋቅር ለሀገራዊ ዓላማ ማሣለጥ፤ ሀገርን በባለ አደራነት መምራት፤ ለምንምና ለማንም የማትበገር ጽኑ ሀገር መገንባት፤ ተተኪ ትውልድን ማፍራት እና የሀገርን ደኅንነት ምንጊዜም ማረጋገጥ” የሚሉትን የሀገራዊ ስትራቴጂው ሐሳቦች በተገቢው መንገድ ለመረዳትም ሆነ ለማስፈጸም ወታደራዊ ሥልጠናው የማይናቅ ሚና ይጫወታል።
ሕዝብን ለታላላቅ ሀገራዊ ዓላማዎች እና ዓላማዎች ማነጽ እንዲሁም ለሕዝብ የተገባውን ቃል በውጤታማነት ማሳካት የሚቻለው ጥብቅ የሥራ ዲሲፕሊን ሲኖር ነው።
ከታች እስከ ላይ ያለውን መዋቅር አንድ ወጥ ለሆነ ሀገራዊ ዓላማ ማሰለፍ፣ ሀገርን በባለአደራነት መምራት እንዲሁም ለምንምና ለማንም የማትበገር ጽኑ ሀገር መገንባትም ጽናት እና ቁርጠኝነትን ይጠይቃል።
እናም የመደመር መንግሥት አመራሮች የሁርሶ ሥልጠና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የሽንገላ ባህል ቀርቶ በውጤት ላይ የተመሠረተ፣ ኃላፊነትን የሚወስድ እና ለታላላቅ ሀገራዊ ዓላማዎች ራሱን የሰጠ አዲስ ትውልድ እየተፈጠረ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: