ከቶኪዮ፣ ከኒውዮርክ፣ ከለንደን ወይም ከሪዮ ዲ ጄኔሮ ተነሥቶ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚደርስ አንድ እንግዳ፣ በእጁ የያዘው ፓስፖርት የየሀገሩን ስም ይዞ ይሆናል። የሚናገረው ቋንቋ፣ የቆዳው ቀለም እና ባህሉም ከእኛ የተለየ ሊሆን ይችላል።
ነገር ግን እግሩ የኢትዮጵያን ምድር በሚረግጥበት በዚያች ቅጽበት፣ ሳይንስ አንድ የማይታበል እውነትን ይመልስለታል፤ “ወደ ባዕድ ሀገር አልመጣህም፤ ወደ ራስህ የዘር ግንድ መነሻ፣ ወደ ቀደመው ቤትህ ተመልሰሃል” ይለዋል።
ዓለም በድንበሮች ከመከፋፈሉ፣ ሀገራት ስም ከማውጣታቸው እና የሰው ልጅ ታሪኩን በብራና እና በወረቀት መጻፍ ከመጀመሩ ከሚሊዮኖች ዓመታት በፊት፣ የኢትዮጵያ መልክዓ-ምድሮች የመላው የሰው ልጅ የጋራ ታሪክ የተጻፈባቸው የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች ነበሩ።
በአፋር እና በኦሞ ምድር የተቀመጠው የዘመን ማኅደር
የሰው ልጅ “ከየት መጣሁ? እንዴትስ ዛሬ ያለኝን ቁመና ያዝኩ?” ለሚሉት ጥንታዊ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት የዓለም ሳይንቲስቶች ፊታቸውን የሚያዞሩት ወደ ኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ነው።
በአፋር ሙቀት እና በኦሞ ተፋሰስ ጥልቀት ውስጥ የሚገኙት ጥንታዊ አፈሮች፣ የሰው ዘር እንዴት ይኖር፣ ይንቀሳቀስ እና ከአካባቢው ጋር ይላመድ እንደነበር የሚያሳዩ ሕያው ማስረጃዎችን እንደ ታማኝ ባለአደራ ጠብቀው አቆይተዋል።
ይህ የሳይንስ ጉዞ በዓለም መድረክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተው እ.አ.አ. በ1974 በአፋር ክልል ሐዳር ውስጥ ነበር። የ3.2 ሚሊዮን ዓመታት ዕድሜ ያላት ድንቅነሽ (ሉሲ) ስትገኝ፣ የዓለምን የሳይንስ ማኅበረሰብ አስደመመች። ‘አውስትራሎፒተከስ አፋሬንሲስ’ (Australopithecus afarensis) የተባለችው ይህችው ቅድመ-አያታችን፣ አፅሟ በ40 በመቶ ገደማ የተሟላ በመሆኑ እስካሁን ከተገኙት የጥንት የሰው ዘሮች (ሆሚኒኖች) ሁሉ እጅግ የተሟላው አፅም ሆኖ ተመዝግቧል።
ድንቅነሽ ለዓለም ያረጋገጠችው ትልቁ እውነት ቢኖር፣ የሰው ልጅ ዛሬ በሚታወቅበት የሆሞ ሳፒየንስ ደረጃ ከመድረሱ ከረጅም ዘመናት በፊት በኢትዮጵያ ምድር ላይ ቀጥ ብሎ በሁለት እግሩ መራመድ መጀመሩን ነው።
ከድንቅነሽ ጎን ለጎን የዓለማችን ጥንታዊቷ ሕፃን “ሰላም” በዚሁ ምድር መገኘቷ፣ ኢትዮጵያ የሰው ልጅ የልጅነትም ሆነ የዕድገት መነሻ መሆኗን አጠናክሮታል።
ታሪኩ በድንቅነሽ አላበቃም። ከድንቅነሽ ግኝት ከሃያ ዓመታት በኋላ፣ በአቅራቢያው በሚገኘው አራሚስ ውስጥ ሳይንቲስቶች የዘመን ስሌትን ወደ ኋላ የመለሰ ሌላ ተዓምር አገኙ፤ አርዲ! በዕድሜው 4.4 ሚሊዮን ዓመታት የሚገመተው እና አርዲፒተከስ ራሚደስ (Ardipithecus ramidus) የተባለው የአርዲ ቅሪተ አካል፣ የሰው ልጅ በዝግመተ ለውጥ የመጀመሪያ ደረጃዎች ላይ የነበረውን የአካል መዋቅር እና አኗኗር በተመለከተ ዓለም ከዚያ በፊት ያላወቃቸውን አዳዲስ ሳይንሳዊ ፍንጮች ሰጠ።
ከጥንታዊው እርምጃ ወደ ዘመናዊው የሰው ልጅ (ሆሞ ሳፒየንስ)
ከሰሜን ምሥራቅ የአፋር ምድር ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ስንጓዝ ደግሞ፣ የኦሞ ተፋሰስ ሌላኛውን የታሪካችንን ወሳኝ ምዕራፍ ይዞ ይጠብቀናል። ዛሬ በዓለም ላይ ያለነው ዘመናዊ የሰው ልጆች (ሆሞ ሳፒየንስ) የቀጥታ መነሻ የሆነው እና እስካሁን በዓለም ላይ ከታወቁት እጅግ አንጋፋው የሆሞ ሳፒየንስ ቅሪተ አካል የተገኘው እዚሁ ኦሞ ውስጥ ነው።
ቢያንስ 233 ሺህ ዓመታት ዕድሜ እንዳለው በሳይንስ የተረጋገጠው ኦሞ 1 (Omo I)፣ ዘመናዊው የሰው ልጅ ራሱን ችሎ ወደ ተቀረው የዓለም ክፍል ከመሰራጨቱ በፊት መነሻው ይህችው የኢትዮጵያ ምድር እንደነበረች ቋሚ ምስክር ነው።
በእነዚህ ተወዳዳሪ በሌላቸው የቅሪተ አካል መዛግብቶቻቸው ምክንያትም፣ ሁለቱም የአዋሽ እና የኦሞ ተፋሰሶች በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (UNESCO) የዓለም ቅርስ መዝገብ ላይ በክብር ሰፍረዋል። ይህ ማለት የአዋሽ እና የኦሞ ሸለቆዎች የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ፣ የ8 ቢሊዮን የዓለም ሕዝብ የጋራ የትውልድ የምስክር ወረቀት የተቀመጠባቸው ስፍራዎች ናቸው።
ከአፅም እና ከቁጥር ባሻገር፦ ይህ ታሪክ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ምን ትርጉም አለው?
እነዚህ ግኝቶች በታሪክ የዘመን ቅደም ተከተል ላይ ስም እና ቀንን ከመጨመር ያለፈ ጥልቅ ፍልስፍናዊ ትርጉም አላቸው። ምድሪቱ ራሷ ሁላችንም የምንጋራውን የጉዞ ማስረጃ ጠብቃ ማቆየቷ፣ የተለያዩ ሕዝቦች እና ሀገራት ከመሆናችን በፊት የአንድ ቤተሰብ፣ የአንድ የሰው ልጅ ታሪክ አካል እንደነበርን ያስታውሰናል።
ዛሬ ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ ትገኛለች። የዓለም መሪዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ የተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋቾች እና ሚዲያዎች የፕላኔታችንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ፣ ጉዟቸው ተራ የዲፕሎማሲ ጉዞ አይደለም። የሰው ልጅ የወደፊት ሕልውናን ለማዳን፣ የሰው ልጅ ሕይወት ወደ ጀመረባት ምድር የሚደረግ ታሪካዊ ምልሰት ነው።
ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ ይህ እውነታ ልዩ ኩራት እና ኃላፊነትን ያሸክመናል፦
1ኛ እንግዶቻችን የሩቅ ሰዎች አይደሉም፦ በጎዳናዎቻችን የምናገኛቸው የCOP32 ተሳታፊዎች፣ ከሚሊዮኖች ዓመታት በፊት ከዚህች ምድር ተነሥተው ዓለምን የሞሉት የቀደሙት ወገኖቻችን ዘሮች ናቸው።
2ኛ የታላቅ ቤተሰብ አስተናጋጆች ነን፦ በባህላችን የታወቅንበት የእንግዳ ተቀባይነት (Hospitality) ከዚህ ሳይንሳዊ እውነታ ጋር ሲዋሃድ፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለእንግዶቹ የሚያሳየው ፈገግታ እና ክብር “እንኳን ወደ ቀደመው ቤታችሁ በሰላም መጣችሁ!” የሚል ትርጉም ይይዛል።
የሰው ልጅ የመጀመሪያውን እርምጃ በድንቅነሽ አማካኝነት በኢትዮጵያ ምድር እንደጀመረ ሁሉ፣ ዛሬ ደግሞ ምድራችንን ከአየር ንብረት አደጋ የማዳኑን ወሳኝ እርምጃ በCOP32 አማካኝነት እዚሁ ኢትዮጵያ ላይ ለመውሰድ ቀጠሮ ይዟል። ታሪክ የጀመረባት ምድር፣ ነገንም ለማዳን ተዘጋጅታለች!
በነቢዩ ወንድወሰን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: