የመደመር መንግሥት ለዘላቂ የሕዝብ ተጠቃሚነት ለያዘው ግብ መሳካት ግብርናን ማዘመን ወሳኝ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
ጥቅምት 22 ቀን 2019 ዓ.ም በቢሮው የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም (FSRP) ድጋፍ የተሠሩ የግብርና ልማት ሥራዎች የመስክ ምልከታ መካሄድ የጀመረ ሲሆን፤ በመርሃ-ግብሩ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ በክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር መንግሥት የዜጎችን ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ በመደመር እሳቤ በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ውጤታማነትን ለማሳደግ እና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በጊዜ የለኝም መንፈስ እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኡስማን፣ ለዚህም ግብርናን ማዘመን እንደ ቁልፍ ስትራቴጂ መያዙን አብራርተዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በክልሉ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ከነበሩበት የዕሳቤና የትግበራ ችግር በማላቀቅ በትክክለኛ መስመር ማስገባት በመቻሉ ውጤታማ እየሆኑ እንደሚገኙ ተገልጿል።
በዚህም በወተት ምርትና ማቀናበር፣ በንብ ማነብና ማር ማቀናበር፣ የእንሰት ምርትና ተዋጽኦ ማቀናበር፣ እንዲሁም በአትክልትና ቅመማ ቅመም ልማት የተሠማሩ 27 ኢንተርፕራዞች ውጤታማ በመሆን ከአባላቶቻቸው በተጨማሪ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ እያደረጉ ይገኛሉ።
እነዚህ ኢንተርፕራይዞች ከምግብ ሉዓላዊነትና ገበያ ከማረጋጋት ባሻገር ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠሩ ሲሆን፣ የፕሮግራሙን አፈጻጸም በሪፖርት ከመገምገም ባሻገር የሕዝብ ተጠቃሚነትን በተጨባጭ ማረጋገጥ በመፈለጉ የመስክ ምልከታው መዘጋጀቱን የቢሮ ኃላፊው አመላክተዋል።
በዚሁ መርሃ-ግብር መሠረት በስልጤ ዞን ምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ በፍረኮት የንብ አንቢዎች ኢንተርፕራይዝ እና የኡሎ ጥጋይ ማር ማቀነባበሪያ ኢንተርፕራይዝ ላይ ምልከታ ተደርጓል።
የስልጤ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙበራ ከማል በዞኑ "የአንድ ወረዳ አንድ ኢንዱስትሪ" የመንግሥት ኢንሼቲቭን ለማሳካት በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝና ለኢንተርፕራይዞቹ ሰፊ የገበያ ትስስር መፈጠሩን ገልጸዋል።
በሁሉም ማዕቀፎች የወጣቶች የሥራ ዕድል ጉዳይ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑ በተገለጸበት በዚህ መርሃ-ግብር ከስራዎች ምልከታ ቀጥሎ የአፈጻጸም ግምገማና ውይይት እንደሚካሄድ ተመላክቷል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: