«ትልቅ ስትሆን ምን መሆን ትፈልጋለህ?» የያኔው የአምስት ዓመቱ ህፃን ቢኒያም ከሞት መንጋጋ፣ ከረሃብና ከእገታ ሰቆቃ ከወጣ በኋላ ለቀረበለት ጥያቄ የሰጠው መልስ አንዲት ቃል ብቻ ነበረች፤ «አየር!» ይህች ቃል የዛሬ ሥድስት ዓመት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመውን የክህደት ጥግ፣ የሠራዊታችንን ጽናት እና ዛሬ መከላከያችን የደረሰበትን የቴክኖሎጂና የአየር ውጊያ ልዕልና አጠቃልይ የያዘች ሕያው ምስክር ናት።
ታሪኩ የሚጀምረው መስከረም 17 ነበር። የሰሜን እዝ አባል የሆነው ምክትል መቶ አለቃ ጌታቸው ፣ ብቸኛ የአምስት ዓመት ልጁን ቢኒያምን የታመመ ዓይኑን ለማሳከም ከወሊሶ ወደ ካምፕ ይዞት ገባ። ሆኖም ለአስራ ሥድስት ዓመታት በትግራይ ምድር ለሕዝብ ሰላም የታገለው ይህ አባት፣ «ወንድሞቻችን ናቸው» ያላቸው የህወሓት ታጣቂዎች ከጀርባ ይወጉናል ብሎ አላሰበም።
የጥቅምት 24 ጨለማ ግን ታሪክ ይዞት የማያውቀውን ክህደት አስተናገደ። ድንበር የሚጠብቀውና ሰብል የሚሰበስበው ሠራዊት በተኛበት ተጠቃ፤ ለሕክምና የመጣው ህፃንና አባቱም በእገታ ውስጥ ወደቁ።
የከሃዲው የሕወሓት ቡድን ጭካኔ ምንም የማያውቅ ህፃንንም ለረሃብና ለሞት የዳረገ ነበር። አባትና ልጅ ከሌሎች ታጋቾች ጋር በመቐለ ዩኒቨርሲቲና በተምቤን ኮሌጅ ያለ ምግብና ውኃ ታጎሩ። ቀጥሎም ዶፍ ዝናብ በህፃኑ ላይ እየወረደ፣ ዝንጀሮ እንኳን የማይወርድበት የወንዝ ገደል ውስጥ እየተነዱ እንዲገቡ ተደረገ።
ከሃዲዎቹ በመኪና አቧራ እያቦኑ፣ ታጋቾቹን በእግር እያስኬዱ ወደ ተዘጋጀላቸው የመቃብር ስፍራ ሲወስዷቸው፣ አባትየውን «ልጁን ለምን እዚህ አትተወውም?» ይሉት ነበር። የአባት መልስ ግን የማይታጠፍ፡- «አይ አልተውም! ቢሞትም ከእኔ ጋር፣ ከሞትኩ ልሙት፣ ከተረፍኩ ልትረፍ! እኔ ከምበላ እሱ ይብላ፣ እኔ ከምጠጣ እሱ ይጠጣ»ነበር፡፡
በዚያ የሞት ጉዞ ላይ ትንሹ ቢኒያም ለታጋች ወታደሮች የሞራል ስንቅ ሆነ። ወታደሮቹ በየተራ በትከሻቸው እየተቀባበሉ ዳገትና ገደል ሲወጡ ለእሱ ሲሉ ያለቅሱ ነበር። እሱ ግን መልሶ «አይዟችሁ!» እያለ ያፅናናቸዋል፤ በተቀመጡበት የልጅ ጨዋታ እያመጣ ሕመማቸውን ያስረሳቸዋል፤ ጠዋት ደግሞ ፊሽካ የነፋ እያስመሰለ «ስፖርት! ሁላችሁም ተነሱ!» ይላቸዋል።
ለአባቱም በጣም አዛኝ ነበር፤ «አባቴ ትደክምብኛለህ፣ በእግሬ ልሂድ» እያለ በጨለማው ውስጥ የፍቅርና የመስዋዕትነት ልኬትን አሳየ።
በጉዞው መካከል አጋቾቹ አባትየውን «ልጅህን እዚያ መኪና ጋቢና ውስጥ አስገባው» አሉት።
አባት ግን ቢደክመውም ልጁን ለጠላት መኪና አልሰጠም። ወዲያው ግን የኢትዮጵያ አየር ኃይል በጠላት ላይ መብረቃዊ ጥቃት ሲሰነዝር፣ ህጻን ቢኒያም ይግባ የተባለበት መኪና ተመቶ ተቃጠለ። ሄሊኮፕተሮችና ጄቶች ሲያንዣብቡና ጭሱ አካባቢውን ሲያውደው፣ ህጻኑ ቢኒያም አፈር ላይ ቁጭ ብሎ እያየ አላለቀሰም። ይልቁንም፦ «የእኛ ነው! መከላከያዎቻችን ናቸው! ሊያተርፉን እየመጡ ነው፣!» እያለ በደስታ መናገሩን አባቱ መናገሩ ይታወሳል።
ከዚያ የሞት ሸለቆ በተአምር የተረፈው አባትም፣ ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ ዳግም ከሠራዊቱ ጋር ተቀላቅሏል። ለዚህም ነበር ቢኒያም ከሞት ተርፎ ምን መሆን እንደሚፈልግ ሲጠየቅ ነፃነቱን የመለሰለትን «አየር!» የመረጠው።
የጥቅምት 24 ክህደት ሀገርንና ሕዝብን በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ ትስስርና በሰው ሕይወት ከፍተኛ ዋጋ ቢያስከፍልም፣ ሠራዊታችንን ግን እንደ ወርቅ በእሳት አነጠረው እንጂ አላፈረሰውም። ዛሬ ከሥድስት ዓመታት በኋላ «ጥቅምት 24 ዳግም እንዳይደገም» የሚለው ቃልኪዳን በተግባር ተተርጉሟል።
ትናንት ህፃን ቢኒያምን የታደገው የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ ዛሬ በዓለም ግንባር ቀደም የሆኑትን የ4++ ትውልድ ሱ-35 (Su-35) የጦር ጄቶችን ታጥቋል። በከፍተኛ ፍጥነት፣ በራዳር የማይደፈር የኤሌክትሮኒክስ ውጊያ አቅምና ዒላማን ከሩቅ በትክክል የመምታት ብቃት ያላቸው እነዚህ ጄቶች፣ ከዘመናዊ የውጊያ ድሮኖች፣ የአየር መከላከያ፣ የሳይበርና የሜካናይዝድ ኃይሎች ጋር ተደምረው የኢትዮጵያን ሰማይና ምድር የማይደፈር የእሳት አጥር አድርገውታል።
የጥቅምት 24ቱ ጠባሳ መቼም አይረሳም፤ ዛሬ ግን የህፃን ቢኒያም ህልም የሆነው «አየር» በሱ-35 የጦር ጄቶች እያገሳ ሉዓላዊነታችንን በኩራት ይጠብቃል። ክህደት ተሸንፏል፤ ኢትዮጵያና መከላከያ ሠራዊቷም በድልና በቴክኖሎጂ ከፍታ ላይ ቆመዋል፡፡
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: