Search

የአፍሪካ ቀጣናዊ ትስስር ማዕከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር ሊቋቋም ነው

ማክሰኞ ጥቅምት 24, 2019 66

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በኤክስፐርቲዝ ፍራንስ መካከል በተደረገው የሶስትዮሽ ስምምነት መሠረት የአፍሪካ ቀጣናዊ ትስስር ማዕከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር እንደሚቋቋም ተገለፀ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ትግበራ እና ከቀጣናዊ ትስስር ጋር የተያያዙ ጥረቶችን ለማገዝ የሚያስችሉ ሁለት የመግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራርሟል።

የመጀመሪያው የመግባቢያ ስምምነት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና በኤክስፐርቲዝ ፍራንስ መካከል የተደረገ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በኤክስፐርቲዝ ፍራንስ መካከል የተፈረመ የሶስትዮሽ ስምምነት ነው።

ኢትዮጵያ እየተገበረች የምትገኘውን ገበያ መር እና በግል ሴክተር የሚመራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያለመ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ለማስቀጠል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር አጀንዳዎች በጠንካራ ተቋማትና በሰለጠነ የሰው ኃይል ሊደገፉ እንደሚገባ በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ወ/ሮ ያስሚን ወሃብረቢ፤ ስምምነቱ ኢትዮጵያ አሁን ላይ በመተግበር ላይ የምትገኘውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ እና የንግድ ትስስር ግቦች ከጠንካራ ተቋማት እና ከሰለጠነ የሰው ሃይል ጋር ማስተሳሰር ወሳኝ ነዉ ብለዋል።

በአውሮፓ ህብረት ፋይናንስ የሚደረገውና በኤክስፐርቲዝ ፍራንስ የሚደገፈው የኢኮ ትሬድ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር አቅም የሚያጠናክር ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በነፃ የንግድ ቀጣናው ውስጥ ንቁ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚና እንድትጫወት፣ የኤክስፖርት ምርቶቿን እንድታሳድግ እና የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ድርድሯን እንድታፋጥን ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በኤክስፐርቲዝ ፍራንስ መካከል በተደረገው የሶስትዮሽ ስምምነት መሠረት የአፍሪካ ቀጣናዊ ትስስር ማዕከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር እንደሚቋቋም ተመላክቷል።

ይህ ማዕከል በንግድ ድርድርና ፖሊሲ ትንተና ላይ ያተኮሩ የሰለጠኑ ሙያተኞችን የሚያፈራና በቀጠናዊ ትስስርና ልማት ልዩ የማስተርስ ትምህርት የሚሰጥ ይሆናል።

ከዚህ ባሻገር በመደመር መንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል መደበኛ የፖሊሲ ውይይቶችን በማመቻቸት ለአፍሪካ የዕውቀት፣ የምርምርና የክህሎት ማዕከል በመሆን የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063ን ለማሳካት እንደሚሰራም ተስፋ ተጥሎበታል።

 

በሳምሶን በላይ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: