Search

የባንዳዎች ሴራ የከሸፈበትና የአገር ህልውና የጸናበት የታሪክ እጥፋት

ማክሰኞ ጥቅምት 24, 2019 64

በታሪካችን ማህደር ውስጥ ከባድ ህመም፣ ድንጋጤ እና ጥልቅ ትምህርት ካስቀመጡ ቀናት መካከል ጥቅምት 24 አንዱ ነው፤ በዛ ቀን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ከእንቅልፋቸው ሳይነቁ፣ ሌሊቱን በሰላም ባፈሰሱት ላብ፣ በሀገር ፍቅር ስሜት ተኝተው በነበረበት ሰዓት የተፈጸመባቸው እጅግ የከረረ ክህደት የማይረሳ ነው።

ህገ ወጡ ህወሓት ለዓመታት አብሮት የቆየውን፣ ህዝቡን ከጠላት ሲጠብቅ የኖረውን፣ ዳር ድንበር እና ሉዓላዊነትን ለማስከበር ዋጋ የከፈለውን ጀግናና የተከበረ ሠራዊት በድንገተኛ ጥቃት ኢላማ ያደረገበት ዕለት ነው ጥቅምት 24፡፡

ባንዳዎች አፋቸውን ሞልተው ክህደቱን መብረቃዊ ጥቃት ሲሉ ስም ሰጡት፤ በደህናው ጊዜ ደረቱን የሰጠላቸውን ከጀርባው ወጉት፤ የፈጸሙት ጥቃት ሰሜን ዕዝ የሚባል ወታደራዊ ካምፕ ላይ ብቻ ከመሰለን ተሳስተናል፤ የህዝብን አብሮነት፣ መተማመን እና የሰላም ምሶሶዎችን ለማናጋት ያለመ ጥቃት ነበር፡፡

ዛሬ ይህን ቀን ስናስታውስ በሀዘን እንድንዋጥ አይደለም፤ አልረሳነውም፤ ግን እንዳይደገም በሚል ጽኑ መርህ ወደፊት ለመራመድ እንጂ።

በርግጥ የሚረሳ አይደለም፤ ቀን በማሳ ሰብል ሲሰበስብ የዋለ ሠራዊት፣ የትግራይን ህዝብ ከመጠበቅ አልፎ ከህዝቡ እንደ አንዱ ሆኖ የኖረን ሠራዊት ድንገት፣ ሳይታሰብ፣ ፖለቲካዊ አላማን ለማሳካት ክህደት መፈጸም በቀላሉ የሚረሳ አይደለም፤ ህመሙ ውስጥ ድረስ ነው፤ ኢትዮጵያዊ ወታደሩን ይወዳል፤ ወታደሩ ሲነካ ያመዋል፤ ለዛ ነው የማንረሳው፡፡

የሰሜን ዕዝ አባላት ከመደበኛ ተልዕኳቸው ጎን ለጎን ከቀናት በፊት በክልሉ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ሲያባርሩ ውለው ከአርሶ አደሩ ጎን እንደሁልጊዜው ቆመው ብዙ ደክመው አሳልፈው እረፍት የወሰዱበት ዕለት ነው ጥቅምት 24፤ ነገር ግን እኩለ ሌሊት ላይ ክህደት መገለጫው የሆነው ህገ ወጡ ቡድን ሰራዊቱ ላይ ታሪክ የማይረሳው አደጋ እየጠነሰሰለት ስለመሆኑ ማንም አልገመተም፡፡

ለሊት ላይ የሰራዊቱ አባላት ካምፕ በድንገተኛ የተኩስ እሩምታ ተናወጠ። ከፊቱ የጠላት ጥይት ሲጠብቅ የኖረው ሠራዊት በዕለቱ ማዕድ አብሮ ከቆረሰው ቆሞ ቀር ሀይል ነበር ጥቃት የተሰነዘረበት። በድንገት መብራትና ግንኙነቶች ተቋረጡ። በጨለማው ውስጥ ማን ከማን ጋር እንደሚዋጋ ለመለየት በማይቻልበት ሁኔታ፣ የዕዙ ዋና ዋና ካምፖችና የመሣሪያ ግምጃ ቤቶች ከበባ ውስጥ ወደቁ። በዕዙ በር ላይ ተረኛ ሆነው የቆሙ ጠባቂዎች ባልተጠበቀ መልኩ ተረሸኑ፤ ከዕንቅልፋቸው ባልነቁ፣ እጃቸው ላይ መሣሪያ ባልነበረ ወታደሮች ላይ ጥይት ዘነበባቸው።

እንግዲህ በታሪክ ውስጥ አንዳንድ ቀናት በድል እና በደስታ አክሊል ብቻ የሚቀዳጁ አይደሉም። ይልቁንም የሀገርን ሕልውና፣ የሕዝብን የጋራ እሴት እና የደኅንነት ምሰሶ እስከ መሠረቱ በሚያናውጡ አሳዛኝ የክህደት አውሎ ነፋሶች የሚዘከሩበት ጊዜም እንዳላቸው ጥቅምት 24 አንዱ ማሳያ ነው፤ ለዛም ነው የማንረሳው።

ጥቅምት 24 በኢትዮጵያ የዘመናዊ ታሪክ ውስጥ አንዱና ትልቁ እጥፋት ነበር፤ በባንዳዎች ምክንያት ኢትዮጵያን ብዙ ዋጋ ያስከፈላት የታሪክ እጥፋት፤ ያን ክህደት ተከትሎ የተቀሰቀሰው የህግ ማስከበር ዘመቻ ብዙ አሳይቶናል፤ በሀገሩ ሉዓላዊነት የማይደራደር ህዝብ መኖሩን፤ ለኢትዮጵያ ደግሞ ደጋግሞ የሚሞትላት ወታደር መኖሩን፤ ፈተናን ወደ ዕድል በፍጥነት መቀየር የሚችል እና በሀገር ብሔራዊ ጥቅም የማይደራደር የመደመር መንግስት እውን እየሆነ መምጣቱን የሚያመላክቱ ብዙ ሁነቶችን የወለደ ነው ጥቅምት 24።

ጦርነት መፍትሔ አለመሆኑን፣ የጥፋት ኃይሎች የሰላምን በር ዘግተው የህዝብን ደህንነት ለአደጋ ሲዳርጉ ሀገር ምን ያህል ፈተና ውስጥ እንደምትወድቅ በግልጽ ታይቷል። ይህ ቀን በደም የተጻፈ ታሪክ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ህዝብና ሰራዊት በፅናት ተነስተው የከፋውን አደጋ ለመመከት ያደረጉት ጥረት የሀገርን ህልውና አስጠብቋል።

ዛሬ፣ ጥቅምት 24ን ስናስታውስ “በቀል” ወይም “ጥላቻ”ን ሰንቀን አይደለም። ይልቁንም እንዳይደገም፤ አንረሳውም በሚል ብሔራዊ ንቁነት ነው። ታሪክን ማስታወስ ማለት ያለፉ ስህተቶችን እና የክህደት ከሰል እንደገና ላለማቀጣጠል ጥንቃቄ ማድረግ ማለት ነው።

ሀዘን መታሰቢያ ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ የጥንቃቄ ደወል ነው። የህወሓት ቡድን የፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት ኢትዮጵያውያንን ከፋፍሎ ለማዳከም የተሞከረበት ቢሆንም፣ ይልቁንም ህዝቡን የበለጠ እንዳይበታተን አስተምሮታል።

በጥቅምት 24 ያየነው የባንዳ ተልዕኮ ዛሬም አለ፤ ታዲያ የባንዳ ተልዕኮ መቼም እንደማይሳካ ጥቅምት 24 ምን ይነግረናል? መልሱ ግልጽ ነው። የሀገርን ክብር ለጠላት አሳልፎ መስጠት፣ ከውስጥ ሆኖ የራስን ወገንና ሰራዊት መወጋት አላፊ ድንገተኛ ጉዳት ቢያደርስም፤ የኢትዮጵያን ህልውና ግን ሊያጠፋው ፈጽሞ አይችልም።

ጥቅምት 24 እንዳይደገም ስንል ተማፅኖ አልያም ማስታወሻ ብቻ አይደለም፤ መሰል የክህደት ድርጊት እንዲደገም ስለማንፈቅድ ነው፤ ጥቅምት 24 እንዲደገም የሚፈልጉ እና የሚታትሩ ይኖራሉ፤ ያ ግን ፈጽሞ የሚሆን አይደለም፡፡

ዛሬ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ትናንት የደረሰበትን በክህደት የተሞላ ጥቃት በመማሪያነት በመጠቀም ራሱን በብቃት፣ በቴክኖሎጂ፣ በስንቅና ዝግጁነት አሻሽሎ የቆመ ኃይል ነው። የሰራዊቱ አቅም አሁን ላይ የሚለካው በቁጥር ብቻ ሳይሆን፤ በማድረግ አቅሙ፣ በጠላት እንቅስቃሴዎች ላይ ባለው ጥልቅ መረጃ የማሰባሰብ እና የቅድመ-ዝግጁነት አቅም ነው።

መሰል ጥቃቶች ዳግም እንዳይከሰቱ ሰራዊቱ እና የሀገሪቱ የጸጥታ መዋቅር በከፍተኛ የዲሲፕሊን መስመር እና በዘመናዊ የጦር አሰራር የተደራጁ ናቸው። የየትኛውም የውጭም ሆነ የውስጥ ኃይል ድንገተኛ ሴራ በሰራዊቱ የንቃት እሳት ቀድሞ የሚከሽፍበት፣ ሉዓላዊነቱንም በብቃት ማስጠበቅ የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

ለሀገር ነፃነት ሲባል የተከፈለው ዋጋ ከንቱ እንዳይሆን፣ እንዳይደገም የሚለው መልዕክታችን የተግባር መገለጫው የዛሬው ጠንካራ፣ ዝግጁ እና ህዝባዊ ሰራዊታችን ነው። ታሪክን አንረሳም፤ ሠራዊታችንን እንጠብቃለን፤ ሰላማችንንም በጽናት እናጸናለን የሚለው በመላው ኢትዮጵያውያን የሚስተጋባ መልዕክት ነው።

ጥቅምት 24 የዕንባና የቁጭት ቀን ብቻ ሳይሆን፣ "ከዚህ በኋላ በጭራሽ!" በሚል ጽኑ ብሔራዊ ቃል ኪዳን የምንተጋበት የድል መሠረት ነው። የባንዳዎች ተልዕኮ ከንቱ ነው፤ የኢትዮጵያ ህልውና እና የሰራዊታችን ክብር ግን ከየትኛውም ጊዜ በላይ ጸንቶ ይኖራል።

 

በቶማስ ሀይሉ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: