Search

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፤ የአፍሪካ አዲስ የታሪክ ማጠፊያ

ረቡዕ ጥቅምት 25, 2019 59

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፍጻሜ አግኝቶ ወደ ሙሉ ሥራ መሸጋገሩ፣ በዘመናዊው የአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ትልቁ የኢኮኖሚ እና የጂኦ-ፖለቲካዊ ውሳኔ መገለጫ ሆኖ ተመዝግቧል።

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ከኃይል ማመንጫ መሠረተ ልማትነት ባሻገር አፍሪካውያን በራሳቸው ሀብት፣ እውቀት እና የጋራ ትጋት ዕድላቸውን በራሳቸው እጅ መቅረጽ እንደሚችሉ ለዓለም ያበሰረ የታሪክ ማጠፊያ ነው።

የሕዳሴ ግድብን ልዩ የሚያደርገው ዋነኛው ምክንያት የውጭ የብድር እና የዕርዳታ ምንጮች ሳይኖሩበት፣ በኢትዮጵያውያን እና በትውልደ-ኢትዮጵያውያን የገንዘብ፣ የጉልበት እና የእውቀት አስተዋጽኦ መገንባቱ ነው።

በሁሉም የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያደረጉት ድጋፍ ፕሮጀክቱን የሕዝባዊ አንድነት እና የመሥዋዕትነት ዓርማ አድርጎታል። ይህ ሂደት ሀገራዊ አቅምን አጠናክሮ ከመጠበቅ ባሻገር፣ "የማይቻል የለም" የሚል አዲስ የሥነ-ልቦና ትንሣኤ በሀገራችን ውስጥ ፈጥሯል።

ግድቡ የኢትዮጵያን የኃይል አቅርቦት በእጥፍ በማሳደግ የሀገራችን የኢኮኖሚ መዋቅር የመቀየር አቅምን እያሳደገው ይገኛል። በታዳሽ ኃይል ላይ የተመሠረተው ይህ ልማት፣ ሀገራችን ለነዳጅ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ በመቀነስ እና ከኃይል ሽያጭ በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ የኢኮኖሚ መረጋጋት እያረጋገጠ ይገኛል።

የሕዳሴ ግድብ ፋይዳ ከኢትዮጵያ ወሰን አልፎ ለአጠቃላይ ምሥራቅ አፍሪካ እና ለቀጣናዊ ውህደት አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። በዚህም ለሱዳን፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የቀጣናውን የኃይል እጥረት እየተቀረፈ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ የምትከተለው መሠረታዊ መርሕ የጋራ ተጠቃሚነት እና በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ላይ የጎላ ጉዳት አለማድረስ የሚለውን ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካውያንን የሥነ-ልቦና ጥገኝነት የሰበረ ትልቅ ምሳሌ ነው። አህጉሪቱ በራሷ የተፈጥሮ ሀብት፣ በራሷ የሰው ኃይል እና የፋይናንስ አቅም እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደምትችል በተግባር አስመስክሯል።

ይህ ስኬት አፍሪካ በአጀንዳ 2063 ያስቀመጠችውን የበለጸገች፣ የተሣሠረች እና የራሷን ዕድል በራሷ የምትወስን አህጉር የመገንባት ራዕይ እውን ለማድረግ የሚያስችል መሠረት ጥሏል።

የሕዳሴው ግድብ ማብራት የጀመረው ኤሌክትሪክ አፍሪካ በራሷ አቅም መቆም እንደምትችል የሚያሳይ አህጉራዊ የትብብር፣ የብልጽግና እና የተስፋ ብርሃን ነው።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: