Search

የትግራይ ቴሌቪዥን ወደ ሥርጭት ተመለሰ

ረቡዕ ጥቅምት 25, 2019 40

“የትግራይ ሚዲያ ኮርፖሬሽን” በሚል አዲስ ስያሜ ሕጋዊ ፈቃድ የተሰጠው የትግራይ ቴሌቪዥን፣ በዛሬው ዕለት ወደ መደበኛ ሥርጭት ተመልሷል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 በተሰጠው ሥልጣን እና ኃላፊነት መሠረት ባደረገው ክትትል፣ የቀድሞው የትግራይ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ የመገናኛ ብዙኃን አዋጁን የሚቃረኑ፣ ብሔራዊ ጥቅምን የሚጻረሩ፣ ጽንፈኝነትን የሚያበረታቱ እና የሀገርን እና የሕዝብን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ይዘቶችን ሲያሠራጭ በመገኘቱ ፈቃዱ መታገዱ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር ተቋሙ ለክልሉ ሰላም እና መረጋጋት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት እና የሕዝብ ድምፅ እንዲሆን በማሰብ ባደረገው ጥረት፣ ተቋሙ በአዲስ መዋቅር እና አቅጣጫ እንዲዋቀር ተደርጓል።

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ለተቋሙ “ትግራይ ሚዲያ ኮርፖሬሽን” በሚል አዲስ ስያሜ የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ የሰጠ ሲሆን፣ ተቋሙ በዛሬው ዕለት ወደ ሥርጭት ተመልሷል።

የትግራይ ቴሌቪዥን ወደ ሥርጭት መመለሱ በክልሉ የሚዲያ አገልግሎት ዳግም እንዲቀጥል ሰፊ ዕድል የሚፈጥር ነው።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: