ከአንድ ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የሚካፈሉበት 2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ከጥቅምት 26 እስከ ጥቅምት 28 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል።
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ አስመልክተው የብልፅግና ፓርቲ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ነቢዩ ስሁል ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
“ለዕድገት መምራት (Governing for Growth)” በሚል መሪ ሐሳብ በሚካሄደው በዚህ አህጉራዊ መድረክ ላይ፣ የገዢ እና ተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ የሀገር መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ምሁራን እንዲሁም የግሉ ዘርፍና የሲቪል ማኅበራት ተወካዮችን ጨምሮ ከ1 ሺህ በላይ ከፍተኛ እንግዶች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።
በብልፅግና ፓርቲ አዘጋጅነት እና በአፍሪካ ገቨርናንስ ሴንተር አስተባባሪነት የሚካሄደው ጉባኤ፣ የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከወቅታዊ የምርጫ ዑደት ባሻገር በሀገር ግንባታ፣ በኢኮኖሚ እድገት እና በፖሊሲ ቀጣይነት ውስጥ የለውጥ ሞተር በመሆን አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ማስቻልን ያለመ ነው።
ተሳታፊዎቹ ለሦስት ቀናት በሚኖራቸው ቆይታ ሁሉም የአፍሪካ ገዢና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለ ረጅም ጊዜ ልማት፣ አህጉራዊ ብልፅግና እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ማረጋገጥ በሚችሉባቸው ቁልፍ ሀገራዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ በሰፊው ይመክራሉ ተብሏል።
ኢትዮጵያ ይህን አህጉራዊ ጉባኤ እንድታስተናግድ የተመረጠችው የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለመሆን እያደረገች ያለችው አዎንታዊ እንቅስቃሴና ፈጣን የልማት ምዕራፍ፣ እንዲሁም ትላልቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎችን በስኬት የማስተናገድ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊና የመሠረተ ልማት አቅም ስላላት መሆኑ ተጠቅሷል።
ጉባኤው ኢትዮጵያን በፖለቲካውም ሆነ በልማቱ ዘርፍ እያስመዘገበች ያለችውን በጎ ተሞክሮ ለአህጉሪቱ መሪዎች ለማካፈልና የአፍሪካን የጋራ እድገት ለማፋጠን መልካም እድል የሚፈጥር ይሆናል።
የመጀመሪያው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ባለፈው ዓመት በጋና አክራ መካሄዱ ይታወሳል።
በዘሃራ መሃመድ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: