በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦትን በማሳደግ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ባለአደራ አስተዳደር ገለጸ።
አሁን ላይ በመቐለ ከተማ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ቀድሞ በነበረው ዋጋ እየቀረቡ መሆኑን ነጋዴዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢቲቪ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል።
በክልሉ ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር የመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች የዋጋ ጭማሪ አሳይተው እንደነበር የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ አሁን ላይ የአቅርቦት መጠን በመጨመሩ ሕብረተሰቡ ቀድሞ በነበረው ዋጋ ሸቀጦችን እየገዛ መሆኑን ጠቁመዋል።
የባለአደራ አስተዳደሩ በክልሉ ወደ ሥራ ከገባ ጀምሮ የመሠረታዊ ፍጆታ ዕቃዎች እጥረት እንዳይከሰት እና ዋጋን ለማረጋጋት በትኩረት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።
በዚህም ባንኮችን ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በጋራ በማወያየት አቅራቢዎች አስፈላጊውን ብድር አግኝተው ሸቀጦችን በበቂ መጠን እንዲያቀርቡ እየተሠራ መሆኑን በባለአደራ አስተዳደሩ የኢኮኖሚ መልሶ ማቋቋም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቴዎድሮስ አረጋይ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በክልሉ ያለውን የነዳጅ እጥረት ለመቅረፍም የነዳጅ አስመጪዎች ከባንኮች በቂ ብድር አግኝተው ነዳጅ እንዲያስገቡ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የባለአደራ አስተዳደሩ ትኩረት አድርጎ ከሚሠራባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የመሠረታዊ ፍጆታ ዕቃዎችን ማረጋጋት መሆኑንም አስታውቀዋል።
በአስማረ ብርሃኑ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: