በታሪክ፣ በነጻነት እና በጽናት ላይ በኩራት የቆመችው ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ ዛሬ ደግሞ የሕዳሴዋን እና የሥራ አቅሟን ፍሬ አፍርታ በዓለም ፊት አዲስ የውበት፣ የብልጽግና እና የከፍታ ታሪክ እየጻፈች ትገኛለች።
የቀደመ ታሪካዊ ግርማዋን ከዘመናዊ የዕድገት ምዕራፍ ጋር በማስተሳሰር የምታደርገው ይህ ሁለንተናዊ የከፍታ ጉዞ፣ የመላው አፍሪካውያን የኩራትና የተስፋ ማዕከልነቷን በአዲስ መልክ ያደሰ ነው።
የዚህ ታላቅ ሀገራዊ ዕይታና እውን እየሆነ የመጣውን ህልም ጥልቅ ሐሳብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት ምሥረታ ላይ “ዛሬ ኢትዮጵያ ‘የአፍሪካ ውብ አበባ' ተብላ ብትጠራ፣ እውነታ እንጂ ባዶ ሙገሳ ተደርጎ አይወሰድም” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ይህ አገላለጽ የተፈጥሮ፣ የታሪክ እና የባህል ጸጋዎቿን ተፈጥሯዊ ድምቀት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሳይሆን፣ በጥበብ፣ በጠንካራ እቅድና በሚያስደምም የጋራ ጥረት እውን እየሆነ ያለውን ሁለንተናዊ ሀገራዊ ለውጥ የሚያበስር እውነታ ነው።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት ምልክት፣ የጥቁር ሕዝቦች የትግል ምሳሌ እና የዲፕሎማሲ መነሻ ከመሆኗም በላይ፣ ዛሬ ላይ በአዲስ የሥራ ባህል፣ በፈጠራ፣ በኢኮኖሚ እና በመሠረተ ልማት ግንባታ እያሳየች ባለው ፈጣን እርምጃ የአህጉሪቱ እውነተኛ ውብ አበባ ሆና በመላው አፍሪካ ፊት አብባለች።
“የአፍሪካ ውብ አበባ” የሚለው ድንቅ ሐሳብ በመደመር ዕሳቤ በላብ፣ በሥራና በትጋት በተመዘገቡ ስኬቶች፣ በሕዝቦቿ ኅብረትና በጋራ ጽናት የተረጋገጠ ህያው እውነታ ነው።
ሀገራችን ያላትን የተፈጥሮ ጸጋ፣ ታሪካዊ ቅርስ፣ የመልክአ-ምድር ውበት እና ያልተነካ የሰው ኃይል አስተባብራ በመጠቀም የአፍሪካ የኩራት፣ የብልጽግና እና የውበት ማዕከልነቷን በየቀኑ በተግባር በማረጋገጥ ላይ ትገኛለች። ይህ የተስፋ፣ የውበትና የከፍታ ምዕራፍ የሁላችንንም የተቀናጀ ጥረት፣ የጋራ ርብርብ እና የጽናት ጉዞ አጠናክሮ መቀጠልን የሚጠይቅ ነው።
በየዘርፉ የምናስመዘግበው ሀገራዊ ስኬት፣ የከተሞች እና የገጠር ልማት እንዲሁም የኢኮኖሚ ጥንካሬ ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለዓለም የምታበራው የብርሃንና የጽናት ወገግታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያደርግ ሲሆን፣ የአፍሪካ ውብ አበባነቷም ለትውልድ የሚሻገር ዘላቂ መሠረት እንዲይዝ ያደርገዋል።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: