የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገራችንን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባሻገር በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በመሳተፍ ለሀገራዊ ክብርና ለዓለም አቀፍ ሰላም የራሱን ዐሻራ አኑሯል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በአፍሪካ ኅብረት ሥር በተከናወኑ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በመሳተፍ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከርና ለአህጉራዊ መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
በእነዚህ ተልዕኮዎች የተሳተፉ የሀገራችን ወታደሮች የከፈሉት መስዋዕትነት የሠራዊቱን ዓለም አቀፍ ኃላፊነት የሚያመላክት ነው። ለአብነትም በኮሪያ ጦርነት የተሳተፉት የኢትዮጵያ ወታደሮች በጀግንነታቸው፣ በውጊያ ብቃታቸው እና በወታደራዊ ሥነ ምግባራቸው የሀገራችንን ስም ከፍ አድርገዋል። ይህ ተሳትፎ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ኃላፊነት የምትወስድ ሀገር መሆኗን ካሳዩ ታሪካዊ ክንውኖች መካከል አንዱ ነው።
በመቀጠልም በኮንጎ ከነጻነት በኋላ በተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ እንዲሁም በሩዋንዳ የተከናወኑ የሰላም ማስከበር እና የሰብዓዊ ጥበቃ ጥረቶች የሠራዊቱን ሰብዓዊ እሴትና ዓለም አቀፍ ኃላፊነት በግልጽ ያሳዩ ናቸው።
በተለይም በአብዬ አካባቢ በተመደበው የተባበሩት መንግሥታት ጊዜያዊ የደኅንነት ኃይል (UNISFA) ውስጥ የኢትዮጵያ ሠራዊት ተሳትፎ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነው። በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን መካከል ባለው ውስብስብ የድንበር ጉዳይ ውስጥ በሰላም ጥበቃ፣ በደኅንነት ማረጋገጥ እና በሰብዓዊ እርዳታ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ለተልዕኮው አስተዋጽኦ አድርጓል።
በተጨማሪም በሶማሊያ የቀጣናውን ደኅንነት የሚፈታተኑ አሸባሪ ቡድኖችን በመመከትና ለሰላም መስፈን በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ የከፈለው መስዋዕትነት የሀገራችንን ለቀጣናዊ ሰላም ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት የሚያመላክት ነው።
የሠራዊቱ ተሳትፎ በውጭ ሀገራት በሚከናወኑ ተልዕኮዎች ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ የሀገራችንን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ዋነኛ ኃላፊነቱ ነው፡፡ ለዚህም ስኬት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል ልማት እና በወታደራዊ ዝግጁነት አቅሙን የማጠናከር ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በልዩ ዘመቻዎች ኮማንዶ 65ኛ ዓመት በዓል ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ "የኛ ዝግጅት በድፍን አፍሪካ ሰላም ለማረጋገጥ፣ በድፍን አፍሪካ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በቀጣናችን ላሉ ሀገራት አለኝታ፣ መከታ ጋሻ ለመሆን ነው" ማለታቸው ይታወሳል። እንዲሁም ኢትዮጵያ የሰላም ምንጭ እንጂ የሌላ ሀገር ወራሪ እንዳልሆነችና ወደፊትም እንደማትሆን በግልጽ አስምረውበታል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሀገር ውስጥ ሉዓላዊነትን ከማስጠበቅ እስከ ዓለም አቀፍ የሰላም ተልዕኮዎች ያለው ተሳትፎ የሀገራችንን የሰላም ዲፕሎማሲና የቀጣናዊ ትብብር አቅም የሚያጎላ ነው።
በተልዕኮዎቹ የተሳተፉ እና መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖች ወታደሮች አስተዋጽኦ በክብር የሚታወስ ሲሆን የሰላም ግንባታ፣ የሀገር መከላከያና የዓለም አቀፍ ትብብር ጥረቶችም የወደፊቱ ትውልድ የሚያጠናክራቸው ሀገራዊ እሴቶች ናቸው።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: