Search

የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሳይንስ የተደገፈው የኢትዮጵያ የግብርና አብዮት

ረቡዕ ጥቅምት 25, 2019 63

ኢትዮጵያ ከሰፊው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ምቹ አግሮ-ኢኮሎጂ፣ ለም መሬት እና የውሃ ሀብቷ አንፃር በአፍሪካ ለግብርናው ዘርፍ ምቹ ሁኔታ ያላት ሀገር ናት። በዚህም የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አልፎ ለሌሎች አፍሪካ ሀገራት ጭምር መትረፍ የሚያስችል አቅም ቢኖርም፣ እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች ያለመጠቀም አሁን ላይ በዘላቂ የልማት ፖሊሲዎች እየተስተካከሉ ይገኛሉ።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ቴክኖሎጂ እና ባዮቴክኖሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር አዲሱ ፈቃዱ (ዶ/ር) ከኢቢሲ ዶትስትሪም ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን እና የሰላም ዋስትናዋን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት በሳይንሳዊ ምርምሮች እና በሀገር በቀል ፀጋዎች ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።

መንግሥት በግብርናው ዘርፍ የጀመራቸው አዳዲስ የልማት ኢኒሼቲቮች በተለይም የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የምግብ ዋስትናን ብቻ ሳይሆን የሥነ-ምግብ ፍላጎትን ጭምር ታሳቢ ያደረጉ በመሆናቸው ለሌሎች አፍሪካ ሀገራት ጭምር ተሞክሮ የሚሆን ትልቅ እመርታ ነው ብለዋል።

በበጋ ወራት ማልማት፣ ጥቅም ላይ ያልዋሉ መሬቶችን ማረስ እና ወንዞችን በሥርዓት መጠቀምን የመሳሰሉ ሥራዎች ሲጠናከሩ ኢትዮጵያ ራሷን በምግብ የምትችልበት ጊዜ እጅግ የቀረበ መሆኑን ጥናቶችን ጠቅሰው አመላክተዋል።

ከ25 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ሕይወት ጋር የተሳሰረው እና ድርቅን የመቋቋም አቅም ያለው "እንሰት" የኢትዮጵያ ትልቁ የሀገር በቀል ፀጋ መሆኑን ገልጸው፣ ይህንን ሀብት በምርምር በማስደገፍ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አዲሱ ፈቃዱ (ዶ/ር) ጠቁመዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በዚህ መስክ ባደረጉት ከፍተኛ ምርምር እናቶችን ከከባድ የጉልበት ብዝበዛ የሚያድኑ እና ከ48 በላይ ማዕከላት የተቋቋሙ ዘመናዊ መፍጫ ማሽኖች ወደ ሥራ ገብተዋል።

በዚህም ከሁለት እና ሦስት ወር በላይ ይወስድ የነበረው ባህላዊ አሠራር፣ በሰባት ቀን ውስጥ እንሰትን ማብላላት የሚያስችል የተፈጥሮ እርሾ ተዘጋጅቶ ለአርሶ አደሩ እየተዳረሰ ይገኛል ብለዋል።

እንደ ሀገር የተጀመሩ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ውጤቶች ወደ ኋላ እንዳይመለሱ ከሀገር ውስጥ ገበያ እስከ ዓለም አቀፍ ፋብሪካዎች የማስተሳሰር ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ተመራማሪው መክረዋል።

እንሰትን በዱቄት መልክ በማዘጋጀት ከጉድጓድ ውጪ በንጽህና ማቀነባበር እና እንደ ቆጮ ኬክ፣ ኩኪስ እና ዳቦ ያሉ ጤናማ ምርቶችን ለገበያ የማቅረብ ሥራዎች ተጀምረዋል። ይህ ሙሉ በሙሉ ሀገር በቀል በሆኑ ግብዓቶች የሚመረተው እንሰት፣ ከሰሃራ በታች ካሉ አፍሪካ ሀገራት ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብን የመመገብ አቅም እንዳለው ዓለም አቀፍ ጥናቶች አረጋግጠዋል።

በእንሰት ቴክኖሎጂ እና በምግብ ደኅንነት ዙሪያ የተሠሩ አዳዲስ ፈጠራዎች አሁን ላይ ከሀገር ውስጥ ባለፈ እንደ ፋኦ ካሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ዕውቅና አግኝተዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የተፈጥሮ ፀጋ በጠንካራ የሥራ ባህልና በቁርጠኝነት መጠቀም ከቻለች የምግብ ዋስትናዋን አረጋግጣ ለቀጣናው እና ለአፍሪካ የምግብ አቅርቦት ማዕከል መሆን ትችላለች።

በላሉ ኢታላ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: