Search

የመደመር መጽሐፍ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ያለው ፋይዳ ትልቅ ነው

ረቡዕ ጥቅምት 25, 2019 63

የመደመር መጽሐፍ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብም ያለው ፋይዳ ትልቅ መሆኑን ከመደመር መጽሐፍ የሩሲያ ቋንቋ ተርጓሚዎች አንዷ የሆነችው ቫላንቲና ኪም ገለጸች፡፡

በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ ሠራተኛ የነበረችውና የ“አር ቲ አፍሪካ” ፕሮዲዩሰር ቫላንቲና ኪም ከኢቲቪ ጋር ባደረገችው ቆይታ፣ የመደመር መጽሐፍ ወደ ሩሲያኛ ቋንቋ እንዲተረጎም ሐሳቡ የመጣው ከአር ቲ አፍሪካ ኃላፊዎች እንደነበር አስረድታለች።

አማርኛ ቋንቋን በሞስኮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ እንደተማረች እና ከዚያም ተመርቃ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በኤምባሲው ውስጥ ለሰባት ዓመታት ማገልገሏን የገለጸችው ቫላንቲና፣ ባለፈው ዓመት ወደ ሞስኮ ተመልሳ በአሁኑ ወቅት በአር ቲ አፍሪካ ላይ እየሠራች እንደምትገኝ ጠቅሳለች።

አማርኛ አቀላጥፋ የምትናገረው ቫላንቲና መጽሐፉ የተተረጎመው የሩሲያ እና የኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከርና አስፈላጊነቱን ለማጎልበት ታስቦ መሆኑን ተናግራለች።

ቫላንቲና መጽሐፉ ከሰባት እስከ ስምንት ዓመታት በፊት የነበረውን የኢትዮጵያን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሁኔታ በሰፊው የዳሰሰ እና በወቅቱ የነበረውን የሀገርን ህልም ወደ እውን የመቀየር ጉዞ ያሳየ አስገራሚ ሥራ መሆኑን ገልጻለች።

የመደመር ፍልስፍና ለአንድ ሀገር ብልጽግና ማምጣት፣ ዜጎች በአብሮነት እንዲያድጉ እና ሀገራቸውን እንዲገነቡ የሚያስችል አጠቃላይ ሐሳብ የያዘ መሆኑን በመጥቀስ፣ መጽሐፉ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አብራርታለች።

ቀደም ሲል በእንግሊዝኛ፣ በአረብኛ እና በቻይንኛ ቋንቋዎች የተተረጎመው የመደመር መጽሐፍ፣ አሁን ደግሞ በሩሲያኛ ተርጓሚዎች እጅ ለዓለም አቀፍ አንባቢያን ቀርቧል።

በሜሮን ንብረት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: