ኢትዮጵያ እውነተኛ የኢኮኖሚ አቅሟን በትክክል የሚመዝን አዲስ እና ዘመናዊ የመለኪያ ሚዛን ይፋ ሆኗል።
የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትሩ በረከት ፍስሐፅዮን እንደገለጹት፣ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት የተገነባውን አዲስ የኢኮኖሚ መዋቅር በአሮጌ ሚዛን ስንመዝን የቆየንበትን አሠራር በመቀየር፣ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርትን (ጂዲፒ) በ2017 በጀት ዓመት ቋሚ መነሻ ዓመት ላይ ተመሥርቶ ወቅታዊ ማድረግ ተችሏል።
ይህ የተካሄደው የስሌት ማሻሻያ የመደመር መንግሥት ኢኮኖሚውን ከመሠረቱ ለመቀየር ያከናወናቸውን ስትራቴጂያዊ ሪፎርሞች ፍሬ በግልጽ ያሳየ ነው።
ቀደም ሲል በነበረው የስሌት ሥርዓት ያልተካተቱት የዲጂታል ኢኮኖሚ እመርታዎች (በቴሌ ብር እና ሞባይል ፋይናንስ በትሪሊዮኖች የሚንቀሳቀስ ገንዘብ)፣ የቴሌኮም ገበያ ለግል ዘርፍ መከፈት፣ የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲመራ መደረጉ፣ የካፒታል ገበያ መመሠረት፣ የኮሪደር እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት እንዲሁም በግብርናው የክላስተር እና የስንዴ ምርታማነት ዕድገት አሁን በአዲሱ ሚዛን ውስጥ በስታቲስቲክስ እንዲጠቃለሉ ሆነዋል።
ሚኒስትሩ ባቀረቡት ይፋዊ መረጃ መሠረት፣ በድሮው ቋሚ ዓመት ስሌት 17.09 ትሪሊዮን ብር (126.5 ቢሊዮን ዶላር) የነበረው የሀገራችን የጠቅላላ ሀገር ውስጥ ምርት መጠን፣ በአዲሱ ወቅታዊ ስሌት በ59.21 በመቶ ከፍ በማለት 24.03 ትሪሊዮን ብር (201.42 ቢሊዮን ዶላር) ደርሷል።
እንዲሁም በ2018 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወደ 31.67–31.86 ትሪሊዮን ብር (210.7 ቢሊዮን ዶላር) ያደገ ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያን ከአፍሪካ አምስተኛው፣ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ደግሞ ሦስተኛው ትልቁ ኢኮኖሚ ያደርጋታል።
የአዲሱ ኢኮኖሚ አወቃቀርም አገልግሎት 35.91%፣ ግብርና 31.57% እና ኢንዱስትሪ 30.2% ድርሻ በመያዝ የተመጣጠነ መዋቅር እንዳለው ያሳያል።
ለዚህ ታሪካዊ የምርመራ እና የስሌት ምዕራፍ የ2017 በጀት ዓመት መነሻ ዓመት ሆኖ የተመረጠበት ምክንያት አንፃራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት የታየበት፣ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ የነበረበት፣ ከምርጫ ዓመት ውጪ መሆኑ እና ከ20 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው የሆነው የኢኮኖሚ ተቋማት ቆጠራ፣ የግብርና ቆጠራ እና የቤተሰብ ፍጆታ ጥናት የተከናወነበት ወቅት በመሆኑ እንደሆነ ተብራርቷል።
ይህ ግዙፍ ሥራ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በባለቤትነት የተከናወነ ሲሆን፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የቴክኒክ ድጋፍ በማግኘት ከዓለም አቀፉ የ2008 የብሔራዊ አካውንት ሥርዓት (SNA) መመዘኛዎች ጋር ሙሉ በሙሉ እንዲጣጣም ተደርጓል።
የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር በረከት ፍስሐፅዮን እንዳሰመሩበት፣ ይህ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ስሌት ማሻሻያ፣ ስሌትን ከእውነታው ጋር በማቀራረብ የፖሊሲ፣ የበጀት እና የኢንቨስትመንት ውሳኔዎች በትክክለኛ ማስረጃ ላይ እንዲመሠረቱ የሚያስችል ነው።
ዜጎች በክብር የሚኖሩባትን እና በራሷ አቅም የምትቆም የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የጋራ ርብርቡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: