የመደመር መንግሥት የጤና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በራስ አቅም የሀገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ የመድኃኒት እና የህክምና መሳርያ አምራች ፋብሪካዎች እንዲጎለብቱ እየሠራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
በወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተገነባውን የኦክስጅን ማምረቻ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል።
ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት፣ ከኮቪድ ወረርሽኝ በፊት እንደ ሀገር ሁለት የመንግሥት እና ስምንት የግል የኦክስጅን ማምረቻ ብቻ እንደነበር አስታውሰው፣ የመደመር መንግሥት ለጤናው ዘርፍ የሰጠው ትኩረት እና የራስ አቅምን ለመሳደግ በተሠሩ ሥራዎች አሁን ላይ የኦክስጅን ማምረቻው ከ65 በላይ መድረሱን ተናግረዋል።
የኦክስጅን እጥረት ማኅበረሰብን ለከፍተኛ እንግልት የሚዳርግ መሆኑን በማንሳት፣ በራስ አቅም የጤናውን ዘርፍ ለማዘመን የሚሠሩ ሥራዎች ዘርፉን የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል።
28ኛው የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤን ምክንያት በማድረግ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራሮች እና የጤናው ዘርፍ ባለሙያዎች በወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና ሌሎች የጤና ተቋማት ላይ ጉብኝት አድርገዋል።
የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤው “ለሉዓላዊና የማይበገር የጤና ሥርዓት” በሚል መሪ ሐሳብ ከትናንት ጀምሮ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ከ1 ሺህ በላይ የጤናው ዘርፍ ተሳታፊዎች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።
በመስከረም ቸርነት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: