Search

በላብ እና በራዕይ የሚታነጽ ሀገር፦ የመደመር መንግሥት እና የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ግንባታ

ሰኞ ጥቅምት 23, 2019 50

ለሺህ ዓመታት የቆሙት የአክሱም ሐውልቶችም ሆኑ የግብጽ ፒራሚዶች፣ የቻይናው ታላቅ ግንብም ሆነ የሱሜሪያ ጥንታዊ ከተሞች የሚመሰክሩት ታላቅ እውነት፣ የሰው ልጅ ሥልጣኔ በምቾት ሳይሆን በመሥዋዕትነት ዕውን መሆኑን ነው። እጅ ሳይላጥ እና ድንጋይ ሳይፈለጥ ለሺህ ዓመታት የሚሻገር ቅርስ ማቆየት የማይቻል መሆኑ እነዚህ ቅርሶች ማሳያ ናቸው።

የኢትዮጵያም ድንቅ ሥልጣኔዎች የዚሁ የአባቶቻችን ብርቱ ትጋት ማኅተሞች ነበሩ። ይሁን እንጂ እነዚህ ገናና ሥልጣኔዎች በውስጣዊ ግጭቶች፣ በመንግሥታት መዳከም እና በአቅርቦት መሳሳት ምክንያት ቀጣይነት አጥተው፣ ከሕያው የዕድገት ሞተርነት ወደ ሙዚየም እና የታሪክ መዘክርነት ተቀይረው ቀርተዋል። ለዘመናት የገጠመን ትልቁ ሀገራዊ አጣብቂኝም በትናንት ገናና ታሪክ እና በዛሬ የድህነት እውነታ መካከል የተፈጠረው ሰፊ ክፍተት ነበር።

የመደመር መንግሥት እሳቤ ይህንን የዘመናት ክፍተት የሞላው ታሪክን እና ሥልጣኔን በአዲስ መነጽር በመተርጎም ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ታሪክ እንደ ወራጅ ወንዝ በራሱ ጊዜ የሚፈስስ ተፈጥሯዊ ሂደት ሲሆን ሥልጣኔ ግን ይህንን ወራጅ ወንዝ መገደብ፣ መቀየስ እና ለዘላቂ ጥቅም ማዋል ነው።

በዚህ ፍልስፍናዊ ዕይታ ዓባይ ለሺህ ዓመታት ሲፈስስ የኖረ ታሪክ ሲሆን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ (የንጋት ሐይቅ) ግን በትውልዱ ክንድ የተገነባ ሕያው ሥልጣኔ ነው።

ኢትዮጵያ ከገባችበት የድህነት እና የኋላቀርነት አዙሪት መውጣት የምትችለው በትናንት ታሪክ በመቆዘም ወይም በመኩራራት ሳይሆን፣ የዛሬን ላብ ከነገ ራዕይ ጋር ደምራ ወራጁን የታሪክ ወንዝ ወደ ልማትና ብልጽግና መቀየር ስትችል ብቻ ነው።

የታሪክ እና የማኅበረሰብ ተመራማሪዎች እንደሚያስረዱት፣ ሥልጣኔ ከውጭ የሚሸመት ሸቀጥ ወይም የሚዋሱት ንድፈ ሐሳብ ሳይሆን አንድ ሕዝብ በውስጥ አንድነት እና በጋራ ማንነት ላይ ተመሥርቶ ለገጠመው ነባራዊ ፈተና የሚሰጠው ሀገር በቀል ምላሽ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመደመር መንግሥት ምሥረታ ላይ “ያለንን የሥልጣኔ ወረት ይዘን፣ የሥነ መንግሥት እሴቶቻችንን አዘምነን፣ በሀገር በቀል እሳቤ ላይ የታነጸ የኢትዮጵያን ሥልጣኔ እንዳንገነባ የሚከለክለን ማነው?” ሲሉ ያነሡት ጥያቄ የዚሁ አዲስ ንቃት መነሻ ነበር።

ዛሬ መደመር የኢትዮጵያ የራሷ የሥልጣኔ ማሰቢያ ቋንቋ ሆኖ ወጥቷል። የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን ሥልጣኔ እየገነባ ነው ማለት፣ ለዘመናት ሀገራዊ ጉዟችንን ጠፍንጎ የያዘውን የአግላይነት እና የነጠላነት ፖለቲካን ትቶ፣ በአካታችነት መርሕ ሀገርን ማሻገር ማለት ነው።

ይህ አዲስ የሥልጣኔ መንገድ ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ እንደ ሀገር መቆየታችንን እንደ ትልቅ መነሻ ወረት በመውሰድ፣ የትናንት በጎ እሴቶችን ሳይጥል እና የውስጥ ስብራቶችን እየጠገነ፣ የዛሬን እውነታዎች አክሎ ወደፊት የሚጓዝ ነው።

የልዩነት ነጠላ መንገድን በመዝጋት ብዝኃነትን ከሀገራዊ አንድነት፣ የግል ፍላጎትን ደግሞ ከጋራ ዕድገት ጋር በማስታረቅ የጋራ ታሪክ እና እሴትን በተግባር እየገነባ ይገኛል። በኢኮኖሚውም መስክ ሀገራችንን ለዘመናት ተብትቦ ከያዛት ነጠላ የኢኮኖሚ መዋቅር በማውጣት ወደ ብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ማሸጋገሩ፣ የመደመር እሳቤ ከንድፈ ሐሳብ አልፎ የሚጨበጥ እና የሚዳሰስ ሥልጣኔ እየወለደ መሆኑን ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡት አስደናቂ ውጤቶች ሕያው ምስክር ናቸው።

ባለፉት ዓመታት በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ ያለፈችው ሀገራችን፣ የውስጥ ስብራቶቿን እየጠገነች እና የውጭ ተጽዕኖዎችን በጽናት እየመከተች አዲሱን የብልጽግና አድማስ ተቀላቅላለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ቢወዷት የምትወደድ፣ ቢጠሏት የምታስፈራ፣ ቢተቿት የማትበገር ድንቅ የታሪክ እና የሥልጣኔ ባለቤት ሀገር ናት። ጠላቶቿ ውድቀቷን ሲመኙ ትነሣለች፤ ድካሟን ሲናፍቁ ጠንክራ ትወጣለች፤ ተበተነች ሲሉ ተሰብስባ ትገኛለች።

አዲሱ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ተነሥቷል። እዚህ ምዕራፍ ላይ ለመድረስ ግን ብዙ ዋጋ ተከፍሏል፤ የተከፈለው እና እየተከፈለ ያለው መሥዋዕትነት ሁሉ ለሀገራችን ዳግም የማይናወጥ የሥልጣኔ መሠረት ለመጣል ነው።

ከሀገር በቀሉ የመደመር እሳቤ የፈለቀው ይህ አዲስ የሥልጣኔ ጉዞ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል እንደሚያረጋግጥልን ኢትዮጵያ የጠላትን ሴራ ሁሉ በጥሳ መሻቷን በተግባር እንደምትከውን፣ እንደምታሸንፍ እና በአዲስ የሥልጣኔ ማማ ላይ ደምቃ እንደምትበለጽግ የሚያበስር ዳግም ትንሣኤ ነው።

በበረከት ሽመልስ                 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: