Search

ወታደራዊ ተቋማት ለሲቪል አስተዳደሩ የሚሰጡት ዕሴቶች ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ናቸው፦ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም

ሰኞ ጥቅምት 23, 2019 66

የፖለቲካል ሳይንስ እና የሕግ ምሁሩ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም  በሁርሶ ወታደራዊ ማሠልጠኛ የተደረገውን የመደመር መንግሥት አመራሮች ሥልጠና አስመልክተው ሰፋ ያለ ጽሑፍ አስፍረዋል።

ፕሮፌሰሩ ጽሑፋቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሕይወት እና አመራር ከወታደራዊ አገልግሎት እና ከዲሲፕሊን ጋር በጥብቅ የተያያዘ መሆኑን በመጥቀስ ይጀምራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ14 ዓመታቸው የነፃነት ታጋይ በመሆን ወታደራዊ ሕይወታቸው መጀመሩን፤ በ17 ዓመታቸው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን መቀላቀላቸውን እና በኋላም የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (INSA) ከመሠረቱ በኋላ በሌተናል ኮሎኔል ማዕረግ ከተከበረው ወታደራዊ አገልግሎት በክብር እስከመሰናበት መቀጠሉን አብራርተዋል።

ከዚያም በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርነት እና በፓርላማ አባልነት ካገለገሉ በኋላ እ.አ.አ በ2018 የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑበት ሂደትን ጠቅሰዋል።

ይህ የታሪክ ሂደት ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ ፕላቶ ‘The Republic’ እና ‘The Laws’ በተሰኙ መጻሕፍቱ ያስቀመጠውን “ሀገር ጠባቂ /ወታደር ዜጋ/” (Citizen-Soldier) ዕሳቤ ጋር የሚሄድ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ። ፕላቶ፣ ሀገርን በሚገባ መምራት እና ማስከበር የሚችሉት አካላዊ ብቃትን ከሞራላዊ እና ፍልስፍናዊ ዕውቀት ጋር ያቀናጁ፣ ለሕዝብ የጋራ ጥቅም የሚቆሙ መሪዎች እንደሆኑ ያስረዳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሁርሶ ወታደራዊ ማሠልጠኛ የታየው የአመራሮች ሥልጠና ዓላማ፣ “በአካል የዳበረ፣ በሞራል የጠነከረ፣ በዕውቀት የተሳለ እና በጥበብ የበሰለ አመራር መገንባት” መሆኑን አስታውቀዋል።

ወታደራዊ ተቋማት ለሲቪል አስተዳደሩ የሚሰጡት የዲሲፕሊን፣ የሀገር ፍቅር፣ የቡድን ሥራ፣ የዓላማ ጽናት እና የተጠያቂነት ዕሴቶች ሀገራዊ ብልጽግናን እና የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆናቸውንም ነው የጠቆመት።

እንደ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገለጻ፣ አንዳንድ ተቺዎች የሁርሶው ሥልጠና “የሲቪል አስተዳደሩን ወታደራዊ የማድረግ አካሄድ ነው፤ የፖለቲካ ታማኝነትን ብቻ ያጠናክራል” የሚል ስጋት ያነሣሉ። ሆኖም ግን ለዚህ የሚሰጠው ምላሽ ግልጽ ነው፦ የሲቪል አስተዳደር አስቸጋሪ እና ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ፈተናውን መቋቋም የማይችል አመራር ቦታውን መልቀቅ ይኖርበታል ሲሉ ያሰምሩበታል።

ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት፣ ከወታደራዊ ሳይንስ የሚቀሰሙ የአመራር ክሂሎቶች ለሲቪል ተቋማት ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው። የቀድሞው የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ጄኔራል ጂም ማቲስ “Call Sign Chaos: Learning to Lead” በተሰኘው መጽሐፋቸው፣ ወታደራዊ የአመራር መመሪያዎች - በምሳሌነት መምራት፣ ሁልጊዜ መማር፣ ትክክለኛ ውሳኔ መስጠት እና ብቁ ቡድን መገንባት - ለሲቪል ተቋማት ውጤታማነት ወሳኝ መሆናቸውን እንደሚያስረዱ ጠቅሰዋል።

የመደመር መንግሥት ግልጽ እና ታላላቅ ሀገራዊ ራዕዮች ያሉት ቢሆንም፣ በየደረጃው የነበሩ የማስፈጸም አቅም ማነስ፣ የቢሮክራሲ እንግልት እና የተቀናጀ አሠራር እጥረት ፈተናዎች እንደነበሩበት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ያነሣሉ።

የሲቪል መሪዎች የሚለኩት በሚናገሩት ራዕይ ሳይሆን ያንን ራዕይ ወደ ተጨባጭ ውጤት የመቀየር አቅማቸው መሆኑን ጠቁመው፣ ስለሆነም የሁርሶው ሥልጠና አመራሩ በከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆኖ ትክክለኛ ውሳኔ የመስጠት፣ የችግር መፍትሔ የማፍለቅ እና ተቋማዊ አፈጻጸምን የማሻሻል አቅሙን ያጎለብትለታል የሚል እምነት አላቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሁርሶው ሥልጠና በግንባር ቀደምትነት በመገኘት ከአመራሮቹ ጋር አብረው ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረጋቸው የታላቅ መሪነት ማሳያ ነው። “በምሳሌነት መምራት” ማለት ለሌሎች ያስቀመጡትን መስፈርት እና ዲሲፕሊን ራስም ወርዶ በተግባር ማሳየት ማለት ነው። ይህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መመሪያ ሰጪ ብቻ ሳይሆኑ ከተመሪዎቻቸው ጋር አብረው የሚደክሙ እና የሚተጉ መሆናቸውን ያሳያል ብለዋል ፕሮፌሰር ዓለማየሁ።

ታላቁ የጦር አበጋዝ ጄኔራል ዳግላስ ማክአርተር “አንድ ጄኔራል ጥሩ ወይም መጥፎ የሚሆነው በሥሩ ባሉት ወታደሮች አቅም ልክ ነው” ማለታቸውን በማስታወስ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የኢትዮጵያ ስኬት የሚለካው በሥሩ ባለው አመራር የማስፈጸም አቅም እና ታማኝነት እንደሆነ አስረድተዋል።

አመራሩ ከሁርሶ ያገኘውን ዲሲፕሊን፣ የቡድን ሥራ እና ሀገራዊ አደራ በመጠቀም የሕዝቡን የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚያቃልሉ፣ አገልግሎት አሰጣጥን የሚያፈጥኑ እና ሀገራዊ ደኅንነትን የሚያረጋግጡ ተጨባጭ ውጤቶችን ማምጣት እንደሚጠበቅበትም አሳስበዋል።

የሁርሶው ሥልጠና ውጤታማነት የሚለካው በሚቀጥሉት ዓመታት በሚመዘገቡ ታላላቅ ሀገራዊ ስኬቶች እና “ኢትዮጵያን ዳግም ታላቅ የማድረግ” ሀገራዊ ራዕይን እውን በማድረግ ነው ሲሉ ሐሳባቸውን ቋጭተዋል።

በዮናስ በድሉ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: