28ኛው የጤና ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ በራሷ ሀብትና ባለሙያዎች የሚመራ፣ ሰው ተኮር እና ተጠያቂነት ያለው ተቋማዊ ሥርዓት የመገንባት ራዕይ እንዳላት ገልጸዋል።
የጤና ሥርዓቱ ወረርሽኞች፣ በአየር ንብረት ለውጥና እና የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ሳይቆራረጥ አገልግሎት የሚሰጥና ለትውልድ የሚሸጋገር የማይበገር እንዲሆን ቃል ኪዳን የተገባበት መሆኑን ሚኒስትሯ አብራርተዋል።
በጉባኤው ያለፉት ዓመታት የጤና ዘርፍ ልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅዶች መጠናቀቃቸው የተገለጸሲሆን፣ ከ2019 እስከ 2021 የፋይናንስ ዓመት የሚተገበረው አዲሱ ስትራቴጂክ ዕቅድ ይፋ ሆኗል።
በቅርቡ በተደረገው ጥናት መሠረት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ 21.2 ሚሊዮን በላይ ሴቶች ዘመናዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ ማግኘት ችለዋል። በተጨማሪም 96 በመቶ እናቶች አራትና ከዚያ በላይ የእርግዝና ክትትል፣ 87 በመቶ ደግሞ በጤና ተቋም የወሊድ አገልግሎት ማግኘታቸው ተገልጿል።
በዚህም የእናቶች፣ ከ5 ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት እና የጨቅላ ሕፃናት ሞት ዝቅ ማለቱ የተገለጸ ሲሆን፣ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ቁጥርም ወደ 224 አድጓል።
በክትባትና በዲጂታል ጤና በኩል በተደረጉ የማካካሻ ዘመቻዎች ከ2.95 ሚሊዮን በላይ ምንም ክትባት ያላገኙ ሕፃናትን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።
እንዲሁም የሄፐታይተስ ቢ እና በ58 ከፍተኛ ጫና ባላቸው ወረዳዎች የወባ ክትባት በይፋ ተጀምሯል። የሥርዓተ-ምግብ መዛባት (መቀንጨር) በ4.7 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፣ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም ተደራሽነት ወደ 540 ወረዳዎች አድጓል።
በተጨማሪም 226 የጤና ተቋማት የኤሌክትሮኒክ ሕክምና መዝገብ የጀመሩ ሲሆን፣ እስከ እ.ኤ.አ 2030 ድረስ 85 በመቶ ተቋማትን ዲጂታላይዝ ለማድረግና የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የሚጠቀም የጤና መረጃ ማዕከል ለማቋቋም ታቅዷል።
ሚኒስትሯ የተመዘገቡት ስኬቶች የሚበረታቱ ቢሆኑም አሁንም በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ የጤና ተደራሽነት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በልዩ እሸቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: