Search

ከሪዮ እስከ አዲስ አበባ፡- የዓለም የአየር ንብረት ዲፕሎማሲእና የኮፕ 32 ተስፋ

ቅዳሜ ጥቅምት 28, 2019 127

ዓለማችን በታሪኳ ከፍተኛውን የበካይ ጋዝ ልቀት፣ አስከፊ የሰደድ እሳት፣ ገዳይ ድርቅ እና እጅግ ሞቃታማ ዓመታትን እያስተናገደች ትገኛለች። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ይህ የሙቀት መጠን፣ የአየር ንብረት ጉዳዮች ቸል ሊባሉ እንደማይችሉና ትብብር ቁልፍ መሆኑን ያሳያል። 

ለዚህም ነው በየዓመቱ ወደ 200 የሚጠጉ ሀገራት የፕላኔታችንን የወደፊት እጣ ፈንታ ለመወሰን በፈራሚ ሀገራት ጉባኤ (COP) ላይ የሚሰበሰቡት። ሳይንስና ፖለቲካ የሚገናኙበት ይህ ወሳኝ መድረክ፣ መነሻውን ያደረገው እ.ኤ.አ. በ1992 በሪዮ ዲ ጄኔሮ በተካሄደው የምድር ጉባኤ (Earth Summit) ላይ ነበር። 

በዚያ ጉባኤ የኢኮኖሚ ልማት ፕላኔቷን ከመጠበቅ ጋር አብሮ መሄድ እንዳለበት ስምምነት ላይ በመደረሱ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስምምነት (UNFCCC) ተፈጠረ፤ ከሶስት ዓመታት በኋላም በርሊን የመጀመሪያውን ጉባኤ (COP1) አስተናገደች።

ጊዜው ከማለፉ በፊት የምድርን ሙቀት መጨመር ለማስቆም በሚደረገው ጥረት፣ መንግሥታት በየዓመቱ በተለያዩ ከተሞች እየተገናኙ በረጅም ድርድሮች የጋራ ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ።

 በዚህ ሂደት የበለፀጉ ሀገራት የበካይ ጋዝ ልቀትን እንዲቀንሱ አስገዳጅ ግብ ያስቀመጠው የ1997ቱ የኪዮቶ ስምምነት፣ የሙቀት ጭማሪን ከ2 ዲግሪ ሴልሺየስ በታችና በ1.5 ዲግሪ ለመገደብ ዓለምን ያስተባበረው የ2015ቱ የፓሪስ ስምምነት እንዲሁም የቅሪተ አካል ነዳጅ አጠቃቀም ደረጃ በደረጃ እንዲቀንስ ጥሪ ያቀረበው የ2021ዱ የግላስጎው ስምምነት ቁልፍ ስኬቶች ናቸው።

በ28ኛው ጉባኤም የታዳሽ ኃይልን በሶስት እጥፍ ለማሳደግና የኃይል ውጤታማነትን በእጥፍ ለመጨመር ግብ የተቀመጠ ሲሆን ፈረንጆቹ 2024 በባኩ ደግሞ ለታዳጊ ሀገራት የአየር ንብረት ጥበቃ ድጋፍ የሚሆን ፍኖተ ካርታ ተነድፏል። በዚህ ሁሉ ጉዞ የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ የተለያዩ አካላት አዲስ የአየር ንብረት ኢኮኖሚ በመቅረጽ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ጉዞው በአማዞን ደን ዳርቻ ወደምትገኘው የብራዚሏ ቤሌም (COP30) አምርቶ፣ ሀገራት ለ2035 የገቡትን ቃል ኪዳን የሚያድሱበትና የፓሪሱ ስምምነት እየሰራ መሆኑን የሚያረጋግጡበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

 በዚህ ዓለም አቀፍ ትግል ውስጥ ኢትዮጵያ የመፍትሔው ግንባር ቀደም መሪ መሆኗን በተግባር እያስመሰከረች ትገኛለች። በተለይም የመደመር መንግሥት ተፈጥሮንና ልማትን የማስታረቅ እሳቤን መሰረት በማድረግ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋንን ያሳደገና ለዓለም አርአያ የሆነ ተሞክሮ ነው።

 ከዚህም ባሻገር መንግሥት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በሌሎች ፕሮጀክቶች የታዳሽ ኃይል አቅምን ማስፋፋቱ፣ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ያደረገው የፖሊሲ ሽግግር፣ የከተማ ኮሪደር ልማቶች እና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን በተጨባጭ ያሳደጉ ታላላቅ ስራዎች ናቸው።

እነዚህ የመደመር መንግሥት ተጨባጭ የአረንጓዴ ልማት ስኬቶች፣ ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) የማዘጋጀት ታሪካዊ ኃላፊነት እንድትጎናጸፍ አስችሏታል። 

ይህ ታላቅ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ፣ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራና በታዳሽ ኃይል የገነባችውን ተሞክሮ ለዓለም የምታጋራበት ከመሆኑም በላይ፣ የአፍሪካን የአየር ንብረት ፍትህና የፋይናንስ ጥያቄዎች ለማሰማት ወርቃማ አጋጣሚ ይፈጥራል።

ከሪዮ እስከ ፓሪስ፣ ከአንታሊያ እስከ አዲስ አበባ (COP32) የሚዘልቀው ጉዞ ዓላማው አንድ ነው፤ እርሱም በዓለም አቀፍ ትብብር ሰዎችን፣ ተፈጥሮን እና የጋራ ነገአችንን መጠበቅ ነው።

ሙሉና ትክክለኛ የጉባኤውን መረጃዎች ከምንጩ ለማግኘት ሁልጊዜም ትክክለኛውን የኮፕ 32 ይፋዊ ድረ-ገጽ https://cop32ethiopia.et/ ይጠቀሙ።

በበረከት ሽመልስ

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: