የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት 2ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ማጠቃለያ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ባስተላለፉት መልዕክት የነቢዩ ዩሱፍ ታሪክ በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ ከሚገኙ ታላላቅ ትምህርቶች አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ታሪኩ የቤተሰብ ፍቅርን፣ ክህደትን፣ መከራን፣ ፈተናን እንዲሁም በእምነትና በፅናት እውነትን ማሸነፍን እንደሚያስተምር ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያም በታሪኳ በርካታ ሤራዎችንና መከዳቶችን አልፋ የተተበተቡባትን ወጥመዶች በሙሉ በመበጣጠስ ወደ ተገባት ክብርና ሥልጣኔ እንደምትመለስ ጽኑ እምነት እንዳላቸው አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በእስልምና ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ ያላት ሀገር መሆኗን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) አሳዳጊ የኡም አይመን፣ የመጀመሪያው ሙአዚን የቢላል፣ የመጀመሪያው ሂጅራ፣ የነጃሺ ምድር እንዲሁም አራተኛዋ የሙስሊሞች ቅዱስ ከተማ ሐረር የሚገኙባት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
ይህንን ታሪካዊና ባህላዊ ቅርስ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ፣ ለቱሪዝምና ለዓለም አቀፍ ግንኙነት በሚገባ መጠቀም እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የመደመር መንግሥት መንፈሳዊነትን እንደ ታላቅ ሀገራዊ ኃይል እንደሚመለከተው ያብራሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህንን ኃይል በአግባቡ በመጠቀም ጠንካራ ሀገረ መንግሥት መገንባት እንደሚቻል እና መንግሥትም የሃይማኖት ተቋማት ጠንካራና ብቁ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
"ለሀገራችን ያልሠራነውን ማንም አይሠራልንም፤ እኛ ያላሳደግናትን ማንም አያሳድግልንም፤ ሰላሟንም ያልጠበቅንላትን ሀገር ማንም አይጠብቅልንም" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም "ለሕዝብ እጅግ የሚጠቅሙ ሰዎች፣ እነርሱ በአላህ ዘንድ እጅግ የተወደዱ ናቸው" የሚለውን አስተምህሮ በማንሳት፣ የሕዝብን ኑሮ፣ ጤና፣ ትምህርትና ሰላም የሚያሻሽል እንዲሁም የኢትዮጵያን የመደመር ሥልጣኔ የሚገነባ በጎ ሥራን በመሥራት ማለፍ እንደሚገባ አደራ ብለዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: