Search

የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ከፋዮችን ቅሬታና ጥቆማ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመቀበል የሚያስችል አዲስ አሰራር ይፋ አደረገ

ቅዳሜ ጥቅምት 28, 2019 93
 
የገቢዎች ሚኒስቴር የሙስና እና የብልሹ አሰራር መከላከል ልዩ የንቅናቄ እቅድ ውይይት ማጠቃለያ እና የመጀመሪያው ሩብ ዓመት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ ባካሄደበት መድረክ የታክስ ከፋዮችን ቅሬታና ጥቆማ በዘመናዊ መንገድ ለመቀበል የሚያስችል አዲስ አሰራር ይፋ አድርጓል።
ይህን አዲስ አሰራር የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ እና የሚኒስቴሩ የኢ-ዳታ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዳዊት ውብሸት ይፋ ያደረጉት ሲሆን ተቋሙ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የአገልግሎት አሰጣጥን እውን ለማድረግ የወሰደው ወሳኝ እርምጃ መሆኑ ተመላክቷል።
የሚኒስቴሩ የመረጃ ቴክኖሎጂ ልማትና አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ኩራቱ ለማ እንደገለጹት ይፋ የተደረገው 6844 ነፃ የጥሪ መስመር ማንኛውንም የገቢውን ዘርፍ አሠራሮችን በተመለከተ ጥቆማዎችን ለመቀበል የሚያስችል ነው።
በዚህ ሥርዓትም ባለጉዳዮች በተቋሙ ሰራተኞች ሥነ-ምግባር ላይ ወይም በማንኛውም አገልግሎት ላይ ቅሬታ ሲኖራቸው በነጻ ማቅረብ የሚችሉ ሲሆን ሲደውሉም የሥነ-ምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት ሠራተኞችን በቀጥታ ያገኛሉ።
በሥራ መደራረብ ምክንያት ስልኩ ባይነሳ እንኳ ሠራተኞቹ ያልተነሳውን ጥሪ አይተው ወደ ባለጉዳዮች በመደወል ጥቆማውን የሚቀበሉበት አሰራር ተዘርግቷል።
ተገልጋዮች ይህንን አገልግሎት ሲጠቀሙ ማንነታቸውን በማሳወቅ ወይም ሳያሳውቁ ቅሬታቸውን ማቅረብ ይችላሉ። ቅሬታው እንደቀረበም ለባለጉዳዮች መከታተያ ቁጥር የሚሰጥ ሲሆን ይህንኑ ቁጥር ተጠቅመው የጉዳያቸውን ሂደት በቅርበት መከታተል እንደሚችሉ አቶ ኩራቱ አብራርተዋል።
በተጨማሪም የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽንን አጠቃላይ አሰራሮች በተመለከተ ቅሬታ ማቅረቢያ ዲጂታል ፖርታል ይፋ ተደርጓል።
በዚህ ፖርታል በኩል የታክስ ከፋዮች የግብር ማስያዣን፣ የዘገየ ተመላሽ ገንዘብን፣ ኢ-ፍትሃዊ ቅጣቶችን፣ የምዝገባ ጉዳዮችን እንዲሁም በሁለቱ ተቋማት አጠቃላይ አገልግሎቶች ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን በዘመናዊ መንገድ ማቅረብ እንደሚችሉ ተገልጿል።
ይህ እርምጃ የታክስ አሰባሰብ ስርዓቱን ማዘመን ብቻ ሳይሆን የአገልግሎት አሰጣጡን ከብልሹ አሰራር የጸዳ በማድረግ የታክስ ከፋዩን ማህበረሰብ እምነትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ሀገራዊ እቅስቃሴ አካል ነው።
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: