በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ 22 ነጥብ የያዘ የአዲስ አበባ ስምምነት መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።
ጉባኤው በአፍሪካ የአስተዳደር ማዕከል (AGC) በተቋቋመው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተነሳሽነት (APPI) ማዕቀፍ፣ ከኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ ጋር በመተባበር የተካሄደ ነው።
በመግለጫው መሠረት አፍሪካውያን መሪዎች ለሕገ-መንግሥታዊ አስተዳደር፣ ለዴሞክራሲያዊ ተጠያቂነት እና ለሰላማዊ የፖለቲካ ውድድር ያላቸው ቁርጠኝነት ተረጋግጧል።
በኢኮኖሚው ዘርፍ የኢንዱስትሪ ልማትን፣ ማኑፋክቸሪንግን፣ ዘመናዊ ግብርናን እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማፋጠን እንደሚገባ አጽንኦት ተሰጥቷል። እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብትን በብቃት በመጠቀም የሀገር ውስጥ የፋይናንስ አቅምን ማጠናከር እና የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።
ለወጣቶችና ለሴቶች የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተሳትፎ ልዩ ትኩረት የተሰጠ ሲሆን፤ በሕዳር 6 ቀን 2026 ዓ.ም. በ16 የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች የፀደቀው «የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቻርተር» ጽድቋል። በ2040 አህጉራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚረዳውን «የኢኒሼቲቭ 2040 አጀንዳ» ማዘጋጀት እና ከአፍሪካ ሕብረት የ2063 አጀንዳ ጋር ማቀናጀት ላይም ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ጉባኤውን በማስተናገድ ላደረገው አስተዋጽኦ ለኢትዮጵያ መንግሥት እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምስጋና ቀርቧል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: